ኢትዮጵያ በቀጣይ አራት ወራት ከመደበኛው በላይ ዝናብ እንደምታስተናግድ ኢጋድ ተነበየ።

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የአየር ንብረት ትንበያ እና ትግበራ ማዕከል ICPAC በቀጣይ አራት ወራት ማለትም ከሰኔ 2016 እስከ መስከረም 2017 ዓ.ም  ኢትዮጵያን ጨምሮ በምስራቅ አፍሪካ የሚኖረውን የዝናብ እና መጠነ ሙቀት ሁኔታ ትንበያ በደቡብ ሱዳን ጁባ ከተማ ይፋ አድርጓል።

ለኢትዮጵያ ክረምት በምንለው እና በሰሜኑ የምስራቅ አፍሪካ ክፍል በክረምት ዝናብ ተጠቃሚ ሀገራት ማለትም ኢትዮጵያ፣ጁቡቲ፣ኤርትሪያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ዮጋንዳና ምዕራብ ኬንያን ጨምሮ በቀጣይ አራት ወራት ከመደበኛው ዝናብ በላይ እንደሚያገኙ የማዕከሉ ባለሞያ የሆኑት ዶክተር ሁሴን ሰዒድ ተናግረዋል።

ሁሴን አክለው በተለይ ለምዕራብ፣ደቡብ ምዕራብ፣ሰሜን፣ሰሜን ምስራቅ፣መካከለኛ የኢትዮጲያ ክፍል መጪው የክረምት በጣም ወሳኝ ወቅት ስለሆነ  ከፍተኛ ኤና ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ ያስተናግዳሉ። በመሆኑም ከሚመጣው ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ አዎንታዊ ተፅዕኖ በመጠቀም ሊያመጣ የሚችለውን አሉታዊ ጉዳት ቀድሞ  መጠንቀቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የቅድመ ጥንቃቄ ክፍተቶች በተለያዮ ጊዜያት በማህበረሰቡ ላይ ጉዳት ሲያስከትሉ ተስተውለዋል የሚሉት አቶ ሁሴን በቀጣይ ክረምትም መሰል ጉዳቶች ከመስተናገዳቸው በፊት በቅድመ ትንበያው መሰረት ከፍተኛ ዝናብ የሚከሰትባቸውን አከባቢዎች በመለየት የቅድመ ጥንቃቄ ስራ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

ቅድመ ትንበያውን መሰረት በማድረግ በጎርፍ ተጋላጭ አከባቢዎች የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎችን መለየት፣ የመረጃውን ማዳረስ፣ዳግመኛ ሰለባ እንዳይሆን መፍትሔዎችን መውሰድ ላይ ከሚመለከተው የመንግስት አካላት ዘንድ ክፍተት መኖሩን ከሳታፊዎች ተነስቷል።