ሌንጮ ባቲ ስለሺ በቀለን ይተካሉ?

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት የቀድሞው የውኃ ሀብት ሚኒስትር ስለሺ በቀለ   ከአምባሳደርነት ሹመታቸው እንዲሁም ከማንኛውም የመንግስት ሃላፊነት  በመልቀቅ በግል  በሙያቸው ለማገልገል ማቀዳቸውን እና ጥያቄ ማቅረባቸውን ሪፖርተር ጋዜጣ መዘገቡ ይታወሳል፡፡ይህንን ተከትሎ አምበሳደር ስለሺ  ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱን ምንጮቻችን ነግረውናል።

አምባሳደር ስለሺ በቀለ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የሥልጣን ዘመን ወቅት የፓርቲ አባል ሳይሆኑ የመንግሥት መዋቅርን መቀላቀላቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ከዚያ አስቀድመው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በውኃ ምኅንድስና ሙያቸው በግል ተቀጥረው ሲያገለግሉ ነበር።

የቀድሞው የአርባምንጭ ዩንቨርሲቲ መምህር ስለሺ በቀለ በአምባሳደርነት ከመሾማቸው በፊት የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ሆነው ከአምስት ዓመት በላይ አገልግለዋል፡፡

አምባሳደር ሽለሺ በታለቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ለዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ቃለ መጠይቅ በመስጠት የሚታወቁ ሲሆን በኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የሶስትዮሽ ውይይቶችንም በመምራት ይታወቃሉ፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ሲያገለገሉ በቆዩት አምባሳደር  ስለሺ በቀለ ምትክ  የወቅቱ የሳዑዲ ዐረቢያ አምባሳደር ሌንጮ ባቲ እንደሚተኩ እየተነገረ ነው፡፡

አምባሳደር ሌንጮ ባቲ በሳዑዲ አምባሳደርነት የተሾሙት በ2013 አጋማሽ ነበር።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣት በኋላ በአማካሪነት፣ በኋላ ደግሞ በአምባሳደርነት እያገለገሉ የሚገኙት ሌንጮ ባቲ፣ የቀድሞ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አንደኛው ክንፍ አመራር ነበሩ።