ሴቶች በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ውስጥ እንዴት ሊሳተፉ ይችላሉ?

በኢትዮጵያ ሴቶች ከአጠቃላይ ማህበረሰቡ ከ50 በመቶ በላይ እንደሚሸፍኑ መረጃዎች ቢያመለክቱም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ያላቸው ተሳትፎ ግን ከቁጥራቸው አንፃር እዚህ ግባ የማይባል እንደሆነ ነው ጥናታዊ መረጃዎች የሚያመለክቱት፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ይህንን ሁኔታ ለመቀየር ሲያስተባብር በቆየው የምክክር ሂደት ውስጥ የሴቶችን ተሳትፎ በሚገባቸው ልክ ለማድረግ ተጨባጭ ስራዎችን ሰርቷል፡፡

የእስካሁኑ የኮሚሽኑ ጥረት እንዳለ ሆኖ ኮሚሽኑ በቅርቡ በሚያስተባብረው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት የሴቶችን ተሳትፎ ከመቼውም ጊዜ በላይ ለማሻሻል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው፡፡

ታዲያ ሴቶች በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ውስጥ እንዴት ሊሳተፉ ይችላሉ?

1. የማህበረሰብ ክፍሎችን በመወከል

በኮሚሽኑ ከተለዩት ባለድርሻ አካላት መካከል የማህበረሰብ ክፍሎች ተጠቃሽ ባለድርሻ አካል ናቸው፡፡ ከእነዚህ የማህበረሰብ ክፍሎች አንዱ ሴቶች ናቸው፡፡ በዚሁ መሰረት ሴቶች ከሚወክሉት የማህበረሰብ ክፍል በተጨማሪ በሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎችም ቢያንስ በ30% መወከል (ተሳታፊ) መሆን እንዳለባቸው ይጠበቃል፡፡

2. የተቋማት (የማህበራት) ተወካይ በመሆን

በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ሴቶች በተቋሞቻቸው እና ማህበሮቻቸው በኩል በሚያገኙት ውክልና መሰረት በሂደቱ ላይ ተሳታፊዎች እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡

3. አወያይ በመሆን

በክልሎች እና የከተማ አስተዳድሮች የሚዘጋጁት አጀንዳን የማሰባሰቢያ መርሐ-ግብሮች በርካታ የውይይት መድረኮች በትይዩ የሚዘጋጁባቸው ሲሆን እነዚህን ውይይቶች የሚመሩ ሰዎች እንደሚያስፈልጉ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ይህንን ከግምት በማስገባት ሴቶች አወያይ በመሆንም ድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው ያምናል፡፡ ስለሆነም ኮሚሽኑ ይህንን ለማሳካት አወያዩች በሚመለበሉበት ጊዜ የሴቶችን እኩል ተሳትፎ ለማረጋገጥ ይሰራል፡፡

ኢትዮጵያ እየመከረች ነው!