የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፤ “አጀንዳ ሊሆኑ ይገባሉ” የሚሏቸውን እና በሃገራዊ ምክክር ላይ ሊቀርቡ የሚገቡ ጉዳዮች እንዲያዘጋጁ ለተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥሪ አቀረበ። ኮሚሽኑ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በሚያቀርቧቸው አጀንዳዎች ላይ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት እና የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት የሚያካሄዱበትን ሁኔታ እንደሚያመቻች አስታውቋል።
ኮሚሽኑ ይህንን ያስታወቀው ለተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በላከው ደብዳቤ ነው፡፡ ኮሚሽኑ ለፖለቲካ ፓርቲዎች በላከው ደብዳቤ፤ ፓርቲዎቹ በሚያቀርቧቸው አጀንዳዎች ላይ “ከሌሎች ባለድርሻ አካላት እና የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመገናኘት ውይይት የሚያካሄዱበትን ሁኔታ በቀጣይ የሚያሳውቅ መሆኑን” አመልክቷል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከባለድርሻ አካላት “አጀንዳዎችን የመሰብሰብ ስራ በማከናወን ላይ እንደሚገኝ” በማንሳት የፖለቲካ ፓርቲዎቹ “ለሀገራዊ ምክክር ሊቀርብ ይገባል” የሚሏቸውን “የአጀንዳ ነጥቦች” የማዘጋጀት ስራ እንዲያከናውኑ በደብዳቤው ጠይቋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከሁለት ሳምንት በፊት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ለሀገራዊ ምክክር የሚሆኑ አጀንዳዎችን የማሰባሰብ ስራ “ባጠሩ ሳምንታት” ውስጥ እንደሚጀምር አስታውቆ ነበር። የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ ተቋማትን እንዲሁም ማህበራትን የሚወክሉ ተወካዮች፤ ከወከላቸው ማህበረሰብ ግብዓቶችን ለማሰባሰብ አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲያደርጉም በወቅቱ ጥሪ ማድረጉ አይዘነጋም።
በታህሳስ 2014 ዓ.ም. በጸደቀው የኮሚሽኑ የማቋቋሚያ አዋጅ፤ የሀገራዊ ምክክር አጀንዳ “በተለያዩ የፖለቲካ እና የሃሳብ መሪዎች፣ በመንግስት እንዲሁም በህብረተሰብ ክፍሎች መካከል፤ ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ያሉ ልዩነቶችን ወይም የአለመግባባት መንስኤዎችን በትክክል የሚዳስሱ ጉዳዮች” መሆናቸውን አስቀምጧል። ኮሚሽኑ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የሚቀርቡለትን እነዚህን አጀንዳዎች ካደራጀ በኋላ ውይይቶች የሚካሄዱባቸውን ርዕሰ ጉዳዮች የመለየት ሚናም በአዋጁ ተሰጥቶታል።
