የብልፅግና ፓርቲ ‘የሚዲያ ሠራዊት’ አባላት በሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት እና አሳሳች የፌስቡክ ዘመቻዎች ላይ መሳተፋቸውን ቢቢሲ በምርመራ ማረጋገጡን ዘግቧል፡፡

በገዢው ብልፅግና ፓርቲ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ስር የሚንቀሳቀሱ እና ‘የሚዲያ ሠራዊት’ የሚል መጠሪያ ያላቸው የፓርቲው አባላት፤ መንግሥትን በሚተቹ እና በሚቃወሙ ግለሰቦች ላይ በፌስቡክ በተደረጉ የሐሰተኛ መረጃ እንዲሁም ‘የጥላቻ ንግግር’ ተብለው ሊቆጠሩ የሚችሉ ጽሑፎች እና ምስሎች ሥርጭት ላይ እንደተሳተፉ ቢቢሲ  በምርመራ ማረጋገጡን ዘግቧል፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወረዳ አመራሮችም በፓርቲው የወረዳ መዋቅሮች ትዕዛዝ በተለይም የመንግሥትን ገፅታ በሰው ሰራሽ መንገድ ለመገንባት ፌስቡክ ላይ በሚደረጉ አሳሳች ዘመቻዎች ላይ እንደሚሳተፉም ተናግሯል፡፡ ቢቢሲ ለዚህ ዘገባ በአዲስ አበባ ከተማ የወረዳ አመራር፣ የፓርቲ አባል እንዲሁም በከተማዋ እና በፌደራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ የሚሰሩ የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች  አነጋግሬያለሁ ያለ ሲሆን የአዲስ አበባ ከተማ ሰባት ክፍለ ከተሞች ውስጥ የሚገኙ የፓርቲው የወረዳ መዋቅሮች በዋትስአፕ እና ቴሌግራም ግሩፖች ውስጥ ለሶሻል ሚዲያ ዘመቻዎች የተለዋወጧቸውን መልዕክቶች መመልከቱም ተዘግቧል፡፡

ቢቢሲ ስለጉዳዩ የፌስቡክ እናት ኩባንያ ሜታ “ሐሰተኛ አካውንቶችን” በመጠቀም “በኢትዮጵያ መንግሥት” የፌስቡክ ልጥፎች ላይ “ብዛት ያላቸው አዎንታዊ አስተያየቶች” መሰጠታቸውን በምርመራ እንደደረሰበት  አስታውቆናል ብሏል። ሜታ፤ በዚህ ድርጊት ላይ በተሳተፉ ሐሰተኛ አካውንቶች እና ገፆች ላይ እርምጃ መውሰዱን  እንዲሁም ቢቢሲ ሲከታተላቸው የነበሩ አካውንቶችም እንዲወገዱ መደረቻቸውንም ቢቢሲ በዘገባው አካቷል።

የብልፅግና ፓርቲ በበኩሉ ‘የሚዲያ ሠራዊት’ የሚባል አደረጃጀት “አለመኖሩን” በመግለፅ ለቢቢሲ በሰጠው የፅሁፍ ምላሽ ጉዳዩን  አስተባብሏል ተብሏል። የፓርቲው ዋና ፅህፈት ቤት፤ “በተለይ ‘ሐሰተኛ መረጃ እና የጥላቻ ንግግር ተብለው ሊቆጠሩ የሚችሉ ጽሑፎች እና ምስሎች ተሠራጭተዋል በሚል የተገለጸው ፍጹም ተቀባይነት የሌለው አገላለጽ ነው” ማለቱን ቢቢሲ ዘግቧል።

 ቢቢሲ ሀሰተኛ ናቸው ካላቸው ዘገባዎች መሃከል ከወራት በፊት ወደ ሃገረ አሜሪካ የተጓዙትን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን ሲኖዶስ ዋና ፀሃፊ   አቡነ ጴጥሮስን በተመለከተ የወጡ ልጥፎች ይገኙበታል፡፡

ጽሁፎቹ “ሰበር መረጃ፤ አቡነ ጴጥሮስ ከሀገር ኮበለሉ”፣ “አሜሪካዊው አቡነ ጴጥሮስ ከሀገር ኮብልለዋል!” እና “ከአሜሪካዊ አቡነ ጴጥሮስ ኩብለላ ጀርባ ያሉ እውነታዎች!” የሚል መግቢያ ያላቸው ናቸው ያለው ቢቢሲ ጽሁፎቹ አቡነ ጴጥሮስን፤ “በቤተ ክህነት ውስጥ ህቡዕ የፖለቲካ አደረጃጀት በመምራት” እና “የቤተክህነት ሃብት የሆነ በርካታ ገንዘብ እና ንብረት ይዞ በመጥፋት” ይከስሳሉ ብሏል።

የኒው ዮርክ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆኑት አቡነ ጴጥሮስ ከሀገር የወጡት፤ “ይፋዊ የሆነውን መደበኛ የአሠራር ሥርዓት ተከትለው” እንደሆነ ቢቢሲ ከቤተ ክርስቲያኗ ያ መረጃ ማግኘቱን ገልጿል።

በዕለቱ ስለ ሲኖዶሱ ዋና ፀሐፊ “መኮብለል” ፌስቡክ ላይ የተሠራጩት ልጥፎች፤ በመደበኛ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች የተሰራጩ የተለመደው ዓይነት የሐሰተኛ መረጃ አልነበሩም። ቢቢሲ ባደረገው ክትትል፤ የመረጃዎቹ ሥርጭት ካለፈው ዓመት ጥር ጀምሮ ከቤተክርስቲያኒቱ ጋር ቅራኔ ውስጥ የገባውን መንግሥት ከመሠረተው ገዢው ብልፅግና ፓርቲ ጋር ግንኙት እንዳለው የሚያሳዩ ማስረጃዎችን አግኝቻለሁ ብሏል፡፡

የሲኖዶስ ዋና ፀሐፊው አቡነ ጴጥሮስ መኮብለላቸውን ከሚገልጹት ጽሁፎች ጋር የተያያዙት ምስሎች ምንጮች መካከል የገዢው ብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ፅህፈት ቤት የወረዳ መዋቅሮች የዋትስአፕ ግሩፖች እንደሚገኙበት ቢቢሲ ባደረገው ክትትል ማረጋገጡም ተዘግቧል። I

አቶ ታዬ ደንደአ እና  ህወሃትም የሃሰተኛ ዘገባው ሰለባዎች እንደነበሩ አረጋግጫለሁ ብሏል ቢቢሲ፡፡

ቢቢሲ በብልፅግና የሚዲያ ሠራዊት ላይ ባደረገው ምርመራ ያገኘኋቸውን  ማስረጃዎች መሠረት አድርጌ ለሜታ ባቀረብኩት ጥያቄ ኩባንያው የተቀናጀ ሐሰተኛ ባህሪ እንቅስቃሴ መኖሩን አረጋግጦ፤ እርምጃ መውሰዱን እና “የአካውንቶች እና የገጾች ስብስብን (a cluster of accounts and Pages)” ማስወገዱን ገልጿልኛል ብሏል።