ከተማዋ በመከላከያ እና በፌደራል ፖሊስ ቁጥጥር ስር ወድቃለች
እታገኘሁ መኮነን
የራያ አላማጣ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሞላ ደርበው መገደላቸውን እና ሌሎች የወረዳው እና የከተማዋ ኃላፊዎች አካባቢውን ለቅቀው ወደ ሌሎች የራያ ወረዳዎች መሄዳቸውን የከተማዋ ከንቲባ አቶ ሃይሉ አበራ ተናግረዋል፡፡
ከተማዋም ከሚያዝያ 7/2016 ዓ.ም. ጀምሮ በመከላከያ ሠራዊት እና በፌደራል ፖሊስ ቁጥጥር ስር መግባቷ ተሰምቷል፡፡
አቶ ሃይሉ የአቶ ሞላ ህልፈትከትግራይ ኃይሎች ጋር በተደረገ “ውጊያ” አይደለም ብለዋል፡፡ በህግ የተያዘ ጉዳይ ስለሆነ ምክንያቱን ለመግለጽ ፍቃደኛ አይደለሁም ብለዋል፡፡
የከተማዋ ነዋሪዎች ከሰኞ ከሰዓት ጀምሮ በርካታ ነዋሪዎች ከተማውን ለቀው በመውጣት ወደ አጎራባች አካባቢዎች መሄዳቸውን ተናግረዋል። አብዛኛዎቹ ነዋሪዎች ወደ ቆቦ ከተማ መግባታቸውም ተሰምቷል፡፡
የራያ አላማጣ ወረዳ እና የአላማጣ ከተማ አስተዳደር ኃላፊዎችም ከሰኞ ጀምሮ አካባቢውን ለቅቀው መውጣታቸውን በአሁኑ ሰዓት ቆቦ እንደሚገኙ የገለፁት የአላማጣ ከንቲባ አቶ ኃይሉ ከትናንት ጀምሮ አላማጣ ከተማን እየተቆጣጠሩ ያሉት የመከላከያ ሠራዊት እና የፌደራል ፖሊስ አባላት መሆናቸውን አስታውቀዋል።
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በበኩሉ ከስህተቱ መማር “የተሳነው” ሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህ.ወ.ሓ.ት) “የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ በመጣስ አራተኛ ዙር ወረራ ሕዝባችን ፈፅሟል” ብሏል፡፡
የአማራ ክልላዊ መንግስት ከባህር ዳር ዛሬ ባወጣው መግለጫ “የማንነት ጥያቄ ያለባቸውን የራያ አላማጣ፣ ራያ ባላ፣ ኦፍላ፣ ኮረምና ዛታ አካባቢዎች ላይ” ህ.ወ.ሓ.ት ወረራ ፈጽሟል ያለ ሲሆን ወረራው የተፈጸመው የአማራ ክልል መንግስት ከፌደራል መንግስት እና ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር ተደጋጋሚ ውይይት ለማድረግ ጥረት እያደረገ በሚገኝበት ወቅት ነው ብሏል።
የአማራ ክልል መንግስት ለክልሉ የፖለቲካና የጸጥታ መዋቅር “እንደ ትናንቱ በፅናትና በቁርጠኝነት ሕዝቡን በማደራጀት አካባቢያችሁን” ጠብቁ ያለ ሲሆን ለክልሉ ሕዝብም “ጠላቶቻችን የከፈቱብንን ጥቃት ለመመከት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ከመንግሥት ጎን” እድንዲሰለፉ ጥሪ አቅርቧል።
