የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር “የአማራ ታጣቂዎች” ያቋቋሟቸውን አስተዳደሮች ለማፍረስ ከፌደራል መንግስት ጋር ተስማምተናል ሲል ተናገረ

በአማራ ታጣቂዎች የተቋቋሙትን አስተዳደሮች ለማፍረስ የፌዴራል መንግስት እና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ከስምምነት ላይ ደርሰዋል ሲሉ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ምክትል ኃላፊ ታደሰ ወረደ ተናገሩ።

አቶ ታደሰ  “የመጀመሪያው እርምጃ በየአካባቢው የታጠቁ ቡድኖችን ማፍረስ እና የተቋቋሙትን ህገ-መንግስታዊ ያልሆኑ አስተዳደሮችን ማፍረስ ሲሆን “የፍትህ ስርዓቱን ወደነበረበት መመለስ” በተከታይነት ይሰራል ብለዋል።

ጄኔራሉ የታጠቁ ሃይሎች ከፌዴራል ሃይሎች ጋር መጠነኛ ግጭት በመፍጠር ሂደቱን እያስተጓጎሉ መሆናቸውንም አብራርተው የፕሪቶሪያ ስምምነት ግጭት እንዳያገረሽ በሚከላከል መልኩ ተግባራዊ ይደረጋል ሲሉ ገልጸዋል።

የጊዜያዊ አስተዳደሩ ምክትል ኃላፊ እንደገለጹት የፕሪቶሪያ ስምምነት የግዛትን ጨምሮ ሁሉም አለመግባባቶች በህገ መንግስቱ መሰረት መፈታት እንዳለባቸው መደንገጉን አስታውሰዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ ግን ትናንት  በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው “በደቡብ ትግራይ እና በሌሎች የትግራይ ግዛቶች የተፈጠረው ግጭት በፌደራል መንግስትና በጊዜያዊ አስተዳደሩ ወይም በህወሓት፤ አሊያም በአማራ እና በትግራይ ክልል አስተዳደሮች መካከል የተፈጠረ አይደለም” ብለው ነበር፡፡

የፕሪቶሪያው ስምምነት እንዲተገበር ለመጠየቅ በራያ አካባቢዎች ቅዳሜና እሁድ የተካሄደውን ሰልፍ ተከትሎ የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ኃይሎች ከፈቱት በተባለው ጥቃት  የተኩስ ልውውጥ መጀመሩን ነዋሪዎች እና የአካባቢውን ባለስልጣናት እየተናገሩ ነው፡፡

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በበኩሉ ህወሓት  በሕዝባችን ላይ አራተኛ ዙር  ወረራ ፈፅሟል” ሲል ትናንት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ ከሷል።

 የአማራ ህዝብ “የቡድኑ ወረራ ቀጥተኛ ሰለባ እና ገፈት ቀማሽ ነው” ያለው አብን፤ የፌዴራልና የአማራ ክልል መንግስታትም በሕዝብ ላይ “የተቃጣውን የጥፋት ወረራ” በአስቸኳይ እንዲያስቆሙ ጥሪውን አቅርቧል።