የኢትዮጵያ እና ኬንያ አትሌቶች ሆን ብለው ቻይናዊ ሯጭ እንዲያሸንፍ በማድረግ ተከሰሱ

አንድ የኢትዮጵያ እና ሁለት ኬንያውያን አትሌቶች ቻይናዊ ሯጭ የቤይጂንግ ግማሽ ማራቶንን እንዲያሸንፍ አድርገዋል ተብለው ምርመራ ተጀመረባቸው።

የውድድሩ አዘጋጅ ቤይጂንግ ስፖርትስ ቢሮ ክስተቱን እየመረመርኩ ነው ሲል ለፈረንሳይ የዜና ወኪል – ኤኤፍፒ ተናግሯል።

ኢትዮጵያዊው አትሌት ደጀኔ ኃይሉ ቢቂላ እንዲሁም ኬንያውያኑ ሮበርት ኬተር እና ዊሊ ማናንጋት ቻይናዊው አትሌት ሂ ጂ እንዲያሸንፍ ያደረጉበት ሁኔታን የተመለከቱ ቻይናውያን “ስፖርታዊ ሥነ ምግባር የሌለበት አሳፋሪ ተግባር” ሲሉ ገልጸውታል።

ሦስቱ አትሌቶች ከውድድሩ መጀመሪያ አንስቶ እስከ ማጠናቀቂያው ድረስ ቻይናዊውያን አትሌት አጅበው ሲሮጡ ነበር።

በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት በተጋራው ቪዲዮ ላይ የውድድሩ መጨረሻ አካባቢ ሦስቱ የምሥራቅ አፍሪካ አትሌቶች ፍጥነታቸውን በመቀነስ ቻይናዊው አትሌት እንዲያልፋቸው በእጃቸው ሲጠቁሙት ይታያሉ።

በመጨረሻም የመላው እስያ ጨዋታዎች የማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊው ቻይናዊ አትሌት ሦስቱን የምሥራቅ አፍሪካ አትሌቶች አስከትሎ በአንድ ሰከንድ ልዩነት ብቻ ውድድሩን አሸንፏል።

የውድድሩ አዘጋጆች ለኤኤፍፒ “ምርመራ እያደረግን ነው። ምርመራችን ሲጠናቀቅ ውጤቱን ይፋ እናደርጋለን” ብለዋል።የውድድሩን ፍጻሜ የሚያሳየው ምስል ዌቦ በተሰኘው በቻይናውያን ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት የተሰራጨ ሲሆን፣ ብዙዎች ቻይናዊው እንዲያሸንፍ ሁኔታዎች ቀድመው የተመቻቹ እንደሆነ ያሳያል እያሉ ነው።

አንድ አስተያየት ሰጪ “ይህ ድል ለአትሌቱ በአትሌቲክስ ሕይወቱ አሳፋሪ ድሉ ሆኖ ይመዘገብለታል” ብሏል።

“ስም ባለው ውድድር ላይ ስፖርታዊ ጨዋነት እንደዚህ ወርዶ ማየት በጣም ያሳፍራል” ብሏል ሌላ አስተያየት ሰጪ።

በቻይና የአትሌቲክስ ውድድር በተለይ በመካከለኛ ገቢ ባላቸው የአገሪቱ ዜጎች ዘንድ ትኩረትን እያገኘ የመጣ ስፖርት ቢሆንም፣ በውድድሮች ላይ ማጭበርበሮችን መመልከት አዲስ አይደለም።

እአአ 2018 ላይ በደቡብ ቻይና በምትገኘው ሸንዠን ከተማ በተደረገው የግማሽ ማራቶን ውድድር ተሳታፊ ከሆኑ 258 አትሌቶች መካከል ግማሽ ያክሉ አቋራጭ መንገዶችን ተጠቅመው አጭበርብረዋል።

የትራፊክ ካሜራዎች አትሌቶች አቋራጮችን እየተጠቀሙ በጫካ ውስጥ ሲሮጡ አሳይተዋል።

በ2019 ደግሞ የዙዋንዙ የሴቶች ዓለም አቀፍ የማራቶን ውድድር ላይ አንዲት ተወዳዳሪ የውድድሩን ከፊል ርቀት ብስክሌት ተከራይታ ስትጋልብ ታይታ ነበር።

በእሁዱ ውድድር ቻይናዊው ሂ ጂ 1፡03፡44 በሆነ ሰዓት ሲያጠናቅቅ ኢትዮጵያዊው ደጀኔ ኃይሉ ሁለተኛ እንዲሁም ኬንያውያኑ አትሌቶች እኩል ሦስተኛ ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል ተብሏል።

ከውድድሩ በኋላ ሂ ለቻይናው ግሎባይል ታይምስ በሰጠው ቃለ መጠይቅ ለፓሪስ ኦሊምፒክ እንዲረዳው ጭምር ጠንካራ ዝግጅት ሲያደርግ እንደነበረ እና በዚህ ድሉ ደስተኛ መሆኑን ተናግሯል።