የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን “አሳፋሪ” የምርመራ ሂደት እየተከተለ ነው – ኦነግ 

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ባወጣው መግለጫ የፓርቲው የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ የነበሩት በቴ ኡርጌሳ ግድያን በተመለከተ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን “አሳፋሪ” የምርመራ ሂደት እየተከተለ ነው ሲል ተናገረ ። 

ኦነግ ትላንት ባሰራጨው መግለጫ፤ ግንባሩ በመንግስት በኩል የሚደረገው “ምርመራ ተዓማነት የጎደለው ፣ የማስረጃ ችግር እና ሀሰተኛ ማስረጃዎችም የቀረቡበት ነው ሲል ተችቷል፡፡

ስለዚህም በባቲ ኡርጌሳ ግድያ ላይ የሚደረገው ምርመራ እየተባለ የሚጠራው መረጃ ከጅምሩ ሆን ተብሎ በተዘበራረቁ በርካታ ማስረጃዎች፣ የተሳሳቱ መረጃዎች እና የሀሰት ዘመቻዎች የተበላሸ መሆኑን ደግመን እንገልፃለን። ሁኔታው በደርግ ጊዜ የነበረውን  የቀይ ሽብር ወቅትን ይመስላሉ ሲል ኦነግ ገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪም በቴ ኡርጌሳ ከእንግዳ ማረፊያው ሲወሰድ የተመለከቱ አንድ የጥበቃ ሰራተኛ ከክስተቱ በኋላ የገቡበት እንዳልታወቀ ኦነግ በመግለጫው አመልክቷል።

ኦነግ የበቴ ኡርጌሳን ግድያ በተመለከተ በማስረጃ አረጋግጫለሁ ያላቸውን ጉዳዮች በዝርዝር አስታውቋል።

  1. በቴ ኡርጌሳ ‘አበበ ጊራዝማ’ ከተባለ የእንግዳ ማረፊያ ክፍላቸው በመንግስት የደህንነት አካላት ተወስደዋል፡፡
  2. ከማረፊያ ክፍሉ ውስጥ እየጎተቱ የወሰዱት የደህንነት ሰዎች ከፍተኛ ድብደባ የፈጸሙበት ሲሆን በሕግ አግባብ እንዲይዙት ሲማጸን እንደነበር አረጋግጠናል፡፡
  3. ድርጊቱን የተመለከተው የእንግዳ ማረፊያው ጠባቂ/ዘበኛ ማስረጃ ለመደበቅ ታፍኗል/ተሰውሯል አልያም ተገድሏል፡፡
  4. ወታደራዊ ዩኒፎርም የለበሱ የደህንነት አባላት በቴ ኡርጌሳን በተሽከርካሪ ላይ ከጫኑ በኋላ ወደ ቆሻሻ ቦታ በመውሰድ ጎትተው ካወረዱ በኋላ እጆቹን አስረው በመጨረሻም በጥይት ተኩሰው እንደገደሉት የአካባቢው ነዋሪዎች አይተዋል። አስክሬኑን በአውሬ ከመበላት ለመጠበቅ በቦታው የነበሩ የአካባቢው ሰዎች ጠፍተዋል ወይም ተገድለዋል፡፡
  5. ከክልሉ መንግስት እና ከብልፅግና ፓርቲ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ቡድኖች ወይም ግለሰቦች ግድያውን ከቤተሰብ ጋር ለማያያዝ በተሳሳተ መንገድ እየሰሩ ስለመሆኑ  አረጋግጠናል፡፡
  6. ባለፉት አምስት ዓመታት ሰላማዊ የፖለቲካ፣ የባህልና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ላይ የተፈጸሙት ግድያዎች  ፍትህ  ስላለገኙ አሁንም በመንግስት በኩል የሚደረገው ምርመራ ምንም ዓይነት ገለልተኛ የመሆን ዕድል እንደሌለው አረጋግጫለሁ ሲል ኦነግ አስታውቋል።

በመጨረሻም የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና የአፍሪካ ሕብረት አካላት እንዲሁም የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቦችና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ገለልተኛ እና ከፓርቲ የጸዳ ምርመራ እንዲያደርጉ ጠይቋል።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በበኩሉ በግድያው ማግስት ባወጣው መግለጫ የተሟላ ምርመራ ተደርጎ ጥፋተኞች ሳይታወቁ የፖለቲካ አቋም ልዩነት በመኖሩ ብቻ ወደመንግስትም ሆነ ሌላ አካል የሚጠቆሙ ጣቶች አግባብ አይደሉም በማለት ግድያውንም እንደሚያወግዝ በመግለጫ አስታውቆ ነበር። ነጻና ገለልተኛ ምርመራ እንደሚደረግም ቃል ገብቶ ነበር።