22/05/2016
በተጠናቀቀው የፈረንጆች 2023 ዓመት በኢትዮጵያ የሙስና ወንጀሎች መጨመራቸውን ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል አስታውቋል።
የ180 አገራት የሙስና ነክ ወንጀሎችን በየዓመቱ የሚመዝነው ተቋም ይፋ ባደረገው የ2023 ሙሉ ዓመት ሪፖርት ኢትዮጵያ በመመዘኛዎቹ 37 ከ100 ነጥብ በማግኘት 98ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡
በተቋሙ መለከያ መሰረት ዓለም አቀፍ አማካኝ የሙስና ውጤት 43 ነጥብ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ከአማካኝ በታች በስድስት ነጥብ ዝቅ ብላ ትገኛለች።
በትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ነጥብ አሰጣጥ መሰረት 100 ማለት ከሙስና ነጻ ማለት ሲሆን ወደ ዜሮ እየቀነሰ ሲሄድ የሙስና ወንጀሎች መጨመራቸውን አመላካች ነው።
ተቋሙ የሚፈትሻቸው የሙስና ዓይነቶች ጉቦ፣ በጀቶችን ማዞር፣ የመንግሥት ስልጣንን ያለከልካይ ለግል ጥቅም ማዋል፣ የመንግስት አካላት በመንግስት ዘርፍ ሙስናን የመቆጣጠር ችሎታ፣ በመንግስት ተቋማት ለሙስና አጋላጭ የሆኑ አሰራሮችን፣ የመንግስት ባለስልጣናት ሃብታቸውን እና ሊፈጠሩ የሚችሉ የጥቅም ግጭቶችን ከማሳወቅ አንጻር፣ የሙስና ጉዳዮች ለሚያጋልጡ አካላት የህግ ከለላ መኖር እንዲሁም በሕዝባዊና መንግስታዊ ጉዳዮች ላይ የመረጃ ማግኘት መብትን ያካትታሉ።
