የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ኦነግ ትላንት ምሽት ባወጣው መግለጫ “የብልጽግና ፓርቲ ወታደራዊ ሃይል” ሲል የጠራው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በኦሮሚያ ክልል ድሮን በመጠቀም በንጹሃን ዜጎች ላይ ወንጀል እየፈጸመ ነው አለ።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኦነግ ባለፈው እሁድ ጥር 12 ቀን 2016 በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ቀርሳ ማሊማ ወረዳ ጊቢሶ ቀበሌ “የድሮን አውሮፕላኖች የመርዝ ጋዝን በመጠቀም” በሠላማዊ ሰዎች ሰፈሮች ላይ የመንግስት ኃይሎች ባደረሱት ጥቃት የበርካታ ሰዎች ህይወት ሲያልፍ የሠላማዊ ዜጎች ንብረት ወድሟል።
ይህን ጨምሮ በሌሎች አካባቢዎችም ጥር 12 እና 13 ቀን 2016 ማለትም እሁድና ሰኞ በተፈጸሙ ጥቃቶች ፓርቲው በስም የጠቀሳቸው አምስት ሰዎችን ጨምሮ “በርካታ ንጹሐን ዜጎች” ሲሞቱ ቁጥራቸው ያልተጠቀሰ የአካል ጉዳት አደጋዎችም ገጥመዋል ተብሏል።
“የብልጽግና ፓርቲ የኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ሰራዊት” እየተባለ የሚጠራው ቡድን “አረመኔያዊነቱን እና ግድየለሽነቱን” በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተደጋጋሚ አሳይቷል ያለው የኦነግ መግለጫ፤ ሰላም ወዳድ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችን ስለሁኔታው ለማሳወቅ ተሞክሯል ብሏል።
የፖለቲካ ድርጅቱ “ሁሉም ሰላም ወዳድ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ይህንን አረመኔያዊ ድርጊት እንዲያወግዙ እንዲሁም በአጠቃላይ በኦሮሚያ ውስጥ ጥቅም ላይ የዋለውን የመርዝ ጋዝ ዓይነት እና መጠን በተለይም ከላይ የተጠቀሱትን ቦታዎች እንዲመረምር ኃላፊነት ላለበት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አካል እንጠይቃለን” ብሏል።
