ኢህአፓ በመቀሌ የፊታችን እሁድ ሊካሄድ ቀጠሮ የተያዘለት ሰልፍ ቀርቷል ተብሎ የሚናፈሰው ወሬ ሃሰተኛ ዜና ነው ሲል አጣጣለ።

አሸናፊ አሰበ

17/04/2016

ህዳር 30/2016 ዓም በአዲስ አበባ እንዳይካሄድ የተከለከለው ሰልፍ የፊታችን እሁድ በመቀሌ ሊካሄድ ቀጠሮ ተይዞለታል። የክልሉ ኮምዩኒኬሽን ሰልፋ እንደማይካሄድ ቢገልጽም ሰልፉን ከሚያስተባብሩት ኮሚቴ አባላት መካከል አንዱ የሆኑት የኢህአፓ ፕሬዚዳንት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዝናቡ አበራ ሰልፉ እንደቀረ የሚወራውን ወሬ ፌክ ኒውስ (fake news) ሲሉ አጣጥለውታል።

መቀሌ ለሚገኘው አስተባባሪ ኮሚቴ የደረሰው ደብዳቤ ሰልፋ ፍቃድ እንደተሰጠው ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ በደብዳቤ ሰልፋ መከልከሉን ያሳወቀ አካል ባለመኖሩ በታቀደለት መሰረት እሁድ ለማካሄድ ዝግጅታችንን እንደቀጠልን ነው ብለዋል

እርሳቸው በመቀሌው ሰልፍ እንደሚገኙ ጥያቄ ያቀረብንላቸው ተ/ፕ ዝናቡ “እግዚአብሔር ያውቃል”  የሚል ምላሻቸውን ሰጥተውናል።

የሰልፋ አስተባባሪ  አባላት አስር ሲሆኑ በአዲስ አበባ ሊካሄድ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው ሰልፍ ከመሰረዙ ቀደም ብሎ አራት የአስተባባሪ ኮሚቴው አባላት በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል።

ከታሰሩት አባላት መካከል አቶ ካልአዩ መሃሪ ከ አንድ ሳምንት እስር በኃላ የተፈቱ ሲሆን የተቀሩት ሦስት አባላት (ጌዴና መድሕን፣አብርሃም ሃይማኖት እና ናትናኤል መኮንን) በአዋሽ አርባ በእስር ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።

ቤተሰብ፣ጠበቃ እና የሃይማኖት አባት እንዳያያቸው መከልከሉን አቶ ዝናቡ የገለጹ ሲሆን ህገመንግስቱ እነርሱ ላይ ሊሰራ አልቻለም ሲሉ ተችተዋል።

አካላቸውን ነፃ የማውጣት መብታቸው እንዲከበር ለልደታ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በታህሳስ 2 ቀን ጥያቄ ማቅረባቸውን እና ፍርድ ቤቱም  ለታህሳስ 5 ፌደራል ፓሊስ ለፍርድቤት እንዲያቀርባቸው ቢያዝም እንዳላቀረባቸው ገልጸዋል።ፍርድ ቤቱ  ፖሊስ ታህሳስ 8 ከዚያም  ታህሳስ 11  እንዲያቀርባቸው ቢያዝም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሰረት ይዞ እየመረመራቸው እንደሆነ በመግለጽ ሳያቀርባቸው እንደቀረ ለአዲስ ጊዜ ተናግረዋል።

የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የታሰሩት አባላት  ዛሬ ረቡዕ ታህሳስ 16/2016 ዓም እንዲቀርቡ ማዘዙ ተሰምቷል።

በተጨማሪም  ሰልፋን  ጥር 5 በአዲስ አበባ ለማካሄድ እውቅና እንዲሰጣቸው ለአዲስ አበባ ከንቲባ ጽ/ቤት በዛሬው ዕለት ደብዳቤ ማስገባታቸውን ከአስተባባሪ ኮሚቴው ሰምተናል።

አዲስ ጊዜ የፍርድ ቤቱን ውሎ እና በድጋሚ እንዲካሄድ ፍቃድ ስለተጠየቀበት ሰልፍ የአዲስ አበባ ከንቲባ ጽ/ቤትን ምላሽ ተከታትለን የምናሳውቅ ይሆናል።