የጣና ሃይቅ እንቦጭ መታረም ከነበረበት ጊዜ በአራት ወራት መዘግየቱ ተነግሯል

አሸናፊ አሰበ

17/04/2016

የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ካለፉት አራት ወራት ወዲህ በአማራ ክልል ውስጥ በተከሰተው የሠላም እጦት ምክንያት የህዳሴ ግድቡ መጋቢና የከተማው እስትንፋስ የሆነው ጣና ሃይቅ ህልውና አደጋ ላይ መውደቁን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
           
ሃይቁን ከዚህ ተግዳሮት ለመታደግ የሚደረገው ጥረት በየጊዜው በክልሉ የሚፈጠሩ የሠላም ችግሮች እየተደናቀፈ ይገኛል ያለው ቢሮው በዚህ የተነሳ የእምቦጭ አረምን ለማጥፋት ሲደረግ የነበረው ጥረት መስተጓጎል ገጥሞታል ብሏል።

ቀደም ሲል በመንግስት ግዥና በተለያዩ ድጋፎች የመጡት የአረም ማስወገጃ መሳሪያዎች አፈር እየበላቸውና ተበላሽተው ከጥቅም ውጭ እየሆኑ እንደሆነ ቢሮው ገልጿል።

ይህንን ተግባር በተልዕኮነት ተቀብሎ የሚሰራው ኤጄንሲም በሠላም ችግር ምክንያት ተንቀሳቅሶ ለመስራት ባለመቻሉ በተለያየ ዘዴ አረሙን በተጨባጭ ለማስወገድ ተጀምረው የነበሩ ጥረቶች ሁሉ በክትትል መጓደል አረሙ እንደገና ወደ ከፋ ስጋትነት መመለሱን ተነግሯል፡፡

መግለጫውን በመመልከት አዲስ ጊዜ ያነጋገረቻቸው የጣና ሃይቅ እና ሌሎች የውሃ አካላት ጥበቃ ልማት ኤጀንሲ ሃላፊ አቶ ፋሲል ድልነሳ እንደገለጹት እንቦጩ በየዓመቱ ክረምቱ ሲወጣ ይታረም እንደነበር ገልጸው በክልሉ ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት አረሙ መታረም ከነበረበት ጊዜ በአራት ወር መዘግየቱን አክለዋል።

ማሽኖቹ የሚገኙት ጣና ሃይቅ ዙሪያ በሚገኙ ማክሰኚት፣ደንቢያ እና ሎሎችም የአማራ ክልል አካባቢዎች ሲሆን በተለይም ከጎንደር አካባቢ የሚገኙትን የማረሚያ መሳሪያዎች ማጓጓዝ በጸጥታው ምክንያት አዳጋች እንደሆነ ለዝግጅት ክፍላችን ገልጸዋል።

እንቦጭ በባህሪው ፈጣን የሆነ የመስፋፋት አቅም ያለው ሲሆን በተለይም በክረምት ወቅት ከሚያገኘው ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ ምክንያት የመስፋፋት አቅሙ እንደሚጨምር ተገልጿል።

አሁን ወቅቱ በክረምቱ ከፍተኛ የዝናብ ስርጭት ምክንያት መጠኑ የሚጨምረው የጣና ሃይቅ የሚጎድልበት እና እንቦጩም በሰው እና በማሽን እገዛ በከፍተኛ ርብርብ የሚታረምበት ወቅት የነበረ ሲሆን ይህ ባለመሆኑ ምክንያት በጣና ሃይቅ ህልውና ላይ ከፍተኛ ስጋት መደቀኑን ሃላፊው ገልፀዋል።