“ተቆርቋሪ ያጣው የንጹሃን ደም በአርያም ይጮሃል” እናት ፓርቲ

ህዳር 20/2016 ዓ.ም

“ተቆርቋሪ ያጣው የንጹሃን ደም በአርያም ይጮሃል” ሲል በሰጠው ርዕስ እናት ፓርቲ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ ንጹሐን ዜጎች ላይ የደረሰውን ጥቃት አስመልክቶ በዛሬው ዕለት መግለጫ አውጥቷል።

ፓርቲው በምሥራቅ አርሲ ሽርካ ወረዳ በሶሌ መድኃኔዓለም እና ሴሮ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ኅዳር 13 ቀን 2016 በተፈጸመ ጅምላ ጭፍጨፋ 27 የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ ንጹሐን ዜጎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን ከአካባቢው ነዋሪዎች መረዳቱን ገልጿል።

“ይኼው ጥቃት ቀጥሎ ኅዳር 17 ቀን 2016 ደግሞ ስምንት ሰዎች በተመሳሳይ መልኩ ሲገደሉ በድምሩ 35 የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ ንጹሐን ዜጎች መገደላቸውን አረጋግጫለው” በማለት ፓርቲው አክሏል።

በርካቶችም ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው የገለጸው ፓርቲው በዚህ ጥቃት ነፍሰጡር ሴትን ጨምሮ ጨቅላ ሕጻናት የተገደሉ ሲሆን 11 ሟቾች የአንድ ቤተሰብ አባላት መሆናቸውን አመላክቷል።

በአካባቢው የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ንጹሐን ዜጎች ላይ መሰል ጥቃት ሲፈጸም በ2016 ብቻ ለአራተኛ ጊዜ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም በከፍተኛ ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ጠቁሟል።

ፓርቲው አክሎም፣ በተለይ የአካባቢው ነዋሪ እራሱን ይከላከልበት የነበረውን ትጥቅ በመንግሥት አመራሮች እንዲፈታ ከተደረገ በኃላ የተፈጸመ ጥቃት መሆኑ መላው ኢትዮጵያውያንን ያሳዘነ ነው ሲል ገልጿል።

ስለሆነም የአካባቢው የመንግሥት አመራሮች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የዚህ የተቀናጀ የጅምላ ጭፍጨፋ ተባባሪ ስለመሆናቸው ከዚህ በላይ ማሳያ ሊኖር አይችልም ሲል ወቅሷል።

ባለፉት አምስት አመታት በሌሎች የኦሮሚያ አካባቢዎች የደረሱት የጅምላ ጭፍጨፋዎች አልበቃ ብለው ዛሬም ይህንን እኩይ ተግባር በመዋቅራዊ አሰራር ማስፈጸም ያለንበትን አሳፋሪ ሥርዓት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል ያለው ፓርቲው፤ ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ስር በሰደደ ጥላቻ ተጠምዶ ጅምላ ጭፍጨፋ መፈጸም በፈጣሪም ሆነ በሕግ ፊት ፈጽሞ ምህረት እንደሌለው ሊታወቅ ይገባል ብሏል።

ይሁን እንጂ “ሥርዓቱ ራሱ የጅምላ ግድያው አቀናባሪ በመሆኑ ለፈሰሰው ደም ፍትህ ይሰጣል ብለን አናምንም፤ ከዚህ ቀደምም ሲያደርግ አልታየም” ማለቱን መግለጫው ያብራራል።

ሆኖም ዛሬ በአርያም የሚጮኸው የጅምላ ግድያ ሰለባ የሆኑ ንጹሐን ዜጎቻችን ደም የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር ፍትህ እንደሚያገኝ አንዳች ጥርጥር የለንም ሲል ገልጿል።

የድርጊቱ አቀናባሪዎችና ፈጻሚዎች ከተጠያቂነት እንደማያመልጡ የገለጸው ፓርቲው “ግጭት ጠማቂ አካላት ከኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮች ላይ በደም የተለወሰ እጃችሁን እንድታነሱ” ሲል አሳስቧል።