ህዳር 30 በአዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍ ተጠራ

ህዳር 19/2016

“ጦርነት ይቁም፣ ሰላም ይስፈን፣ መከላከያ ሰራዊቱ በአስቸኳይ ወደካምፕ ይግባ” በሚል መሪ ቃል ለህዳር 30 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍ መጠራቱን አዲስ ጊዜ ማረጋገጥ ችላለች፡፡

ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት የሰላማዊ ሰልፍ እና የአደባባይ ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍል የገባው የሰልፍ ጥሪ ደብዳቤ እንደሚያብራራው፣ ሰልፉ ከተዘጋጀበት ዋንኛ ዓላማዎች መካከል ቀዳሚው “የመከላከያ ሰራዊቱ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል ውስጥ በመግባት ደም አፋሳሽ ተግባር ውስጥ በመሆኑ ከተሰጠው የሀገር ሉዓላዊነት የማስጠበቅ ሚና ውጭ ከሚያደርገው ዘመቻ በመቆጠብ ወደጠቅላይ ጦር ሰፈሩ እንዲገባ የሚጠይቅ” ነው፡፡

የሰላማዊ ሰልፉ አስተባባሪዎች በደብዳቤው ላይ እንደገለጹት የጥሪው ዓላማዎች መከላከያ ሰራዊቱን የሚመለከቱ ብቻ ሳይሆኑ፣ “በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ እንዲሁም በሲዳማ ክልሎች በሚገኙ የተለያዩ ቦታዎች በአማራ ተወላጅነታቸው ምክንያት ያለምንም ፍርድ በየማጎሪያዎቹ ታፍነው የሚገኙ ዜጎችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስራት እንዲፈቱ ለማሳሰብ” ብሎም “በኦሮሚያ፣ በአማራ እና በትግራይ ክልሎች የሚገኙ ተፈናቃዮች የማንም የፖለቲካ ቁማር መጫወቻ መሆናቸው እንዲቆም፣ በአስቸኳይ ወደቀያአቸው እንዲመለሱ ለመጠየቅ” ያሰቡ ናቸው፡፡

በመጪው ህዳር 30 ቀን ሊካሄድ በታቀደው በዚህ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ በግምት 100 ሺህ ሰዎች እንደሚገኙበት እና የአዲስ አበባ ፖሊስም ህገመንግስታዊ ግዴታውን እንዲወጣ በደብዳቤው ላይ ተመላክቷል፡፡ ይህን ሰልፍ ከሚያስተባብሩት መካከል የቀድሞ የኢዜማ ሊቀመንበር የሺዋስ አሰፋ፣ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ከፍተኛ አመራር የነበሩት ጌታነህ ባልቻ እንዲሁም የኢሕአፓ ፕሬዘዳንት እና ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ 13 ፖለቲከኞች እንደሚገኙበት የታወቀ ሲሆን የእነዚህ ፖለቲከኞች ስም ከነፊርማቸው በደብዳቤው ላይ ሰፍሯል፡፡