አውሮፓዊያን እና አሜሪካ ተባብረው እያስፈራሩኝ ነው ስትል ኢትዮጵያ ወቀሰች፡፡

ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ 18 ምዕራባውያን ሀገራት  እና ኢምቢሲዎች እና የአሜሪካ ኤምባሲ ‘የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀንን’ አስመልክተው ባሳለፍነው ሳምንት ባወጡት የጋራ መግለጫ የኢትዮጵያን የጋዜጠኞች አያያዝ መተቸታቸው ይታወሳል፡፡

አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ ብሪታንያ፣ ጀርመን፣ ስዊድን፣ ቤልጂየም፣ ኖርዌይ፣ ስፔን፣ ኔዘርላንድ እና ሌሎች የአውሮፓ ህብረት ሃገራት በጋራ ባወጡት መግለጫ  ኢትዮጵያ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን እንድታከብር ጠይቀዋል፡፡

ሀገራቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ጋዜጠኞች ስራቸውን በመስራታቸው “ማስፈራሪያ እና እስር ይደርሰባቸዋል” ሲሉ በመግለጫቸው ላይ ጠቅሰውም ነበር።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር  ቃል አቀባይ አቶ ነብዩ ተድላ በዚህ ዙሪያ ለጋዜጠኞች  በሰጡት መግለጫ  ምዕራባዊን ሀገራት በቡድን መግለጫ በማውጣት  ሊያስፈራሩን ሞክረዋል   ሲሉ ተናግረዋል፡፡

“ኢትዮጵያ መግለጫውን ካወጡት እያንዳንዳቸው ሀገራት ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት አላት፣ ግንኙነታችን የሚመራው በዚህ ሆኖ ሳለ በኢትዮጵያ ጉዳይ መግለጫ በቡድን ማውጣት እንደ ማስፈራራት ይቆጠራል” ብለዋል አቶ ነብዩ።

ከሰሞኑ የትግራይ ታጣቂዎች ከሱዳን ብሔራዊ ጦር ጋር ተሰልፈው የፈጥኖ ደራሽ ሀይሎችን እየወጉ ነው በሚለው መረጃም ላይ አቶ ነብዩ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ቃል አቀባዩ በምላሻቸው ጉዳዩን እንደሰሙ ነገር ግን እንደ ሀገር ኢትዮጵያዊያን ታጣቂዎች በሱዳን ጦርነት ውስጥ መሳተፍ አለመሳተፋቸው እየተጣራ መሆኑን ተናግረዋል።

“ታጣቂዎቹ በሱዳን ጦርነት መሳተፍ አለመሳተፋቸው ከተጣራ በኋላ መረጃውን ይፋ እናደርጋለን” ሲሉም አቶ ነብዩ በምላሻቸው ላይ ጠቅሰዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የአውሮፓ ህብረት መኖሪያ ፈቃድ ሳይኖራቸው በአውሮፓ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ኢትዮጵያ ተባባሪ አይደለችም በሚል ያሳለፈው ውሳኔ ተገቢነት የጎደለው እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው ላይ እንዳሉት “የአውሮፓ ህብረት 86 ሰዎች ኢትዮጵያዊያን ናቸው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ አድርጉ ሲሉን መጀመሪያ እነዚህ ዜጎች ዜግነታቸው ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን ማረጋገጥ አለብን በሚል ባደረግነው ማጣራታም 26ቱ ብቻ ኢትዮጵያዊ ሆነው ተገኝተዋል” ብለዋል።

በአውሮፓ ሀገራት ይኖሩ የነበሩ እና የመኖሪያ ፈቃድ ካላገኙ መካከል 15 ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ መደረጉንም አቶ ነብዩ ተናግረዋል።

ይህን ሁሉ ጥረት እያደረግን ህብረቱ ኢትዮጵያ ተባባሪ አልሆነችም በሚል በኢትዮጵያውያን ቪዛ አመልካቾች ላይ የቪዛ ገደብ መጣሉ አግባብ ነው ብለን እናምንም ሲሉም ቃል አቀባዩ አክለዋል።