የ2023 የአፍሪካ የምጣኔ ኃብት ጉባዔ በመጭው ሕዳር ወር በኢትዮጵያ ይካሄዳል

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር በመተባበር የሚያሰናዳው የ2023 የአፍሪካ የምጣኔ ሃብት ጉባዔ በኢትዮጵያ እንደሚካሄድ ተነገረ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በመጭው ሕዳር ወር የሚከናወነው የአፍሪካ የምጣኔ ሃብት ጉባዔ በአካል እና በድረ ገጽ በቅይጥ መልኩ እንደሚሰናዳ የገለጸ ሲሆን፤ አካላዊው መድረክ ደግሞ አዲስ አበባ በሚገኘው የመንግሥታቱ ድርጅት አዳራሽ እንደሚካሄድ አስታውቋል።

የአህጉሪቱ ትልቁ የምርምር እና የምጣኔ ሃብት መሰባሰቢያ የሆነው ይህ መድረክ የአህጉሪቱን ሚኒስትሮች፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተባባሪዎች እና ቁልፍ የሆኑ የመንግሥት እና የግልም ኩባንያዎች ወኪሎች እንዲሁም እውቅና ጀማሪ ተመራማሪዎችን ያሳትፉበታል ተብሏል።

ጉባዔው መከናወን የጀመረው በግሪጎሪያን አቆጣጠር በ2006 ሲሆን፤ በዚህ ዓመት በዘላቂ ኢንዱስትሪያላይዜሽን ላይ ትኩረቱን እንደሚያደርግ ተነግሯል።