የሰላም እጦት ግብር የመሰብሰቡን ስራ አዳጋች አድርጎታል ሲል የአማራ ክልል አስታወቀ

ጥቅምት 20/2016

 የአማራ ክልላዊ መንግስት በዘንድሮ በጀት ዓመት 71 ነጥብ 61 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ ወደ ስራ የገባ ቢሆንም በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት በሩብ ዓመቱ መሰብሰብ የቻለው 6 ቢሊዮን 264 ሚሊየን ብቻ መሆኑን አስታወቀ።

አብዛኛዎቹ የክልሉ ዞኖች እና ከተማ አስተዳደሮች የሚጠበቅባቸውን ገቢ በመሰብሰብ ረገድ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ የክልሉ የገቢዎች ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ፍቅረማሪያም ማሳሰባቸውን ከክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ የማህበራዊ ትስስር ገጽ ላይ የተገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡

ገቢ ከሌለ የህክምና ተቋማት እና ት/ቤቶች ይዘጋሉ፤ የመንግስት ሠራተኞች ደመወዝ ይቆማል፤ ልማት፣ እድገት፣ ብልጽግና አይኖርም ሲሉ የክልሉ የገቢዎች ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ፍቅረማሪያም ደጀኔ መናገራቸውን መረጃው አካቷል።

በ2016 በጀት ዓመት 71 ነጥብ 61 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ሥራ የተጀመረ ቢሆንም በክልሉ የተፈጠረው የሠላም ዕጦት እና የቁርጥ ግብር ጥናቱ የወሰደው ረዘም ያለ ጊዜ የታሰበው ገቢ ላለመሰብሰቡ ምክንያት ነው ያለው መረጃው በዚህም በሩብ ዓመቱ 6 ቢሊዮን 264 ሚሊየን 985 ሺህ 447 ብር ወይም የዕቅዱን 34 በመቶ ብቻ መሰብሰብ መቻሉን አመላክቷል፡፡

ይህም ከባለፈው ተመሳሳይ በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ2 ቢሊየን 140 ሚሊየን 398 ሺህ 891 ብር ያነሰ መሆኑን ተያይዞ የወጣው መረጃ ጠቁሟል።