ሐቅን ፍለጋ

መረጃ የምናገኝበት አማራጭ አድጓል፡፡የምናገኛቸው መረጃዎች በሙሉ ግን የተጣሩ እና ትክክለኛ  መሆናቸውን  የማረጋገጥ ልማዳችን ግን ገና ነው፡፡የጋዜጠኛ ሥራ መሰረቱ እውነታን በማጣራት እና በማረጋገጥ ላይ የተመሰረተ ቢሆንም ተሰራጭተው የምናገኛቸው መረጃዎች ሁሉ ግን በጋዜጠኞች እና ኃላፊነት በሚሰማቸው መገናኛ ብዙሃን የተዘጋጁ አይደሉም።

አሁን ኢትዮጵያን ከሚፈትኑ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የተዛቡ መረጃዎች  ስርጭት ነው፡፡በተለያዩ ጊዜዎች የተከሰቱ ግጭቶችን  እና ወቅታዊ ጉዳዮችን ተከትሎ ደግሞ እነዚህ የመረጃ መዛባቶች እና ሀሰተኛ መረጃዎች ይበራከታሉ፡፡ኢትዮጵያ 7ኛውን ጠቅላላ ሃገራዊ ምርጫ ለማድረግ ስትዘጋጅ አንደኛው ስጋቷ የነበረው ይሀው ጉዳይ ነበር።የምርጫ ወቅቶች የሚኖሩ መረጃዎች የመራጮች ውሳኔ ላይ በቀጥታም በተዘዋዋሪም ተፅእኖ ይኖራቸዋል፡፡

አዲስ ጊዜ ሐቅ ለማጣራት የእውነት ማጣሪያ አምድን  በድረገጹ አዘጋጅቷል፡፡ይህ የእውነት ማጣሪያ እኛ ከምናያቸው መረጃዎች በተጨማሪ  እውነት የማጣራት ስራን የሚሰሩ( Fact-checkers)  ስራዎቻቸውን እንዲያሳትሙም ለማድረግ የታሰበ ነበር፡፡በዚህ መሃል ነበር ሀገራዊ ምርጫ የደረሰው፡፡

በአንድ ሀገር ላይ ሁለንተናዊ ለውጥ ለማምጣት ትልቅ አቅም ያለውን ምርጫ  የምታደርግ ሀገር ጤናማ የመረጃ ፍሰት እና አውድ ሊኖራት ይገባል ብለን እንደ ባለሙያ እናምናለን።የመረጃ መዛባትን ለመከላከል ፍላጎት ብቻውን በቂ አይደለም፡፡በምርጫ ጊዜ ሊኖሩ የሚችሉ የመረጃ አይነቶችን፣ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮች እና ቅድመዝግጅቶችን ማወቅ ይጠይቃል።ያገኘናቸውን የተሳሳቱ መረጃዎች የምናጣራበት መንገድ እና የምናጣራባቸው መሳሪያዎች እውቀት ይጠይቃሉ።እነዚህን እውቀቶች እና ልምዶችን ደግሞ አፍሪካ ፋክት ቼኪንግ አሊያንስ እና ኮድ ፎር አፍሪካ በሰጡን የስልጠና እድል ማሳካት ችለናል።ስልጠናው መረጃዎችን እንዴት መመርመር እንዳለብን ፣በየትኞቹ መሳሪያዎች  (Tools )ተጠቅመን ማጣራት እንዳለብን በዝርዝር ተግባራዊ እና ንድፈ ሀሳባዊ እውቀት እና ክህሎት አግኝተናል።በተለይም የሰውሰራሽ አስተውሎትን AI  በመጠቀም የሚሰሩ ሀሰተኛ ቪዲዮዎች እና ምስሎችን የምናጣራበትን መንገድ በተለያዩ ምሳሌዎች እና ተግባራዊ ልምምድ ተመልክተናል።

ፍጹም ለእውነትነት የቀረቡ የሚመስሉ የተዛቡ መረጃዎችን ለመለየት ከመሳሪያዎቹ ባለፈ የግል ምልከታ እና ለነገሮች ያለን ግንዛቤ ትልቅ ድርሻም እንዳለው ተገንዝበናል።ከዚህም በተጨማሪ በመረጃ ማጣራት ሂደት ወስጥ መጀመሪያ የመረጃው ምንጭ ከየት እንደሆነ መለየት አስቸጋሪ የሚሆንበት አጋጣሚ እንደሚፈጠር እና በዚህ ሁኔታ ውስጥ መረጃ እንዴት መጣራት እንዳለበት የሚያሳዩ መንገዶችን አይተናል።

የሚሰራጩ የሀሰተኛ መረጃዎች በአንድ አጋጣሚ የሚፈጠሩ ሃይማኖታዊ ጉዳዮችን፣ግጭቶችን እና ወቅታዊ ትኩሳቶችን እንደመነሻ  እንደሚጠቀሙ በእነዚህ ዘገባዎች ላይ ታይተዋል።መረጃዎችን ከስር ከስር ከማጣራት ባሻገር ዜጎች ያዩትን መረጃ ከማመን፣ ከመቀበል እና ከማጋራታቸው  በፊት ቆም ብለው እንዲያስቡ የሚያደርጉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ይበልጥ መስራት እንዳለብን ይሰማናል።

በአፍሪካ ፋክት ቼኪንግ አሊያንስ እና ኮድ ፎር አፍሪካ  በኩል በተደረገልን ሙያዊ ድጋፍ እና ክትትል ያጣራናቸው እነዚህ መረጃዎች ለስራችን ትልቅ መሰረት ናቸው።ከዚህ በኃላ በቋሚነት ስራችንን በየጊዜው እንድንሰራ ያደርገናል።ከዚህ በኃላ ምርጫን በተመለከተ ለሚኖሩ ዘገባዎችም ምሳሌ ይሆናል ።ግንቦት እና ሰኔ ላይ የነበረው ቆይታችን ከምርጫ በፊት በምርጫ ወቅት እና ከምርጫ በኃላ የሚያጋጥሙ የመረጃ መዛባቶችን ለይቶ የማጣራት ክህሎትን አግኝተናል።የሐቅ ማጣሪያችንንም ስራ አስጀምረናል።አፍሪካን ፋክት ቼኪንግ አሊያንስስ (ኤ.ኤፍ.ሲ.ኤ) የዘርፉ ባለሞያዎችን ለማብቃት የሚሰራውን ስራ በእጅጉ እናደንቃለን።  ከኮድ ፎር አፍሪካ፣ ፔሳቼክ የሰጠን የአቻ ለአቻ ስልጠና ስራችንን ውጤታማ አድርጎታል።