በምርጫ ወቅት እውነት ሲጣራ

የሀሰተኛ መረጃዎች ስርጭት ሁሉም በተለያየ መልኩ ሊኖሩ ይችላሉ።ሀገራት ምርጫ በሚያደርጉበት እና ግጭቶች በሚከሰቱበት ወቅት ሀሰተኛ መረጃዎች ከሌላው ጊዜ በተለየ ጨምረው ይስተዋላሉ።እነዚህ በተለያዩ ይዘቶች የሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎች ማጣሪያ ስይደረግባቸው ከቀጠሉ ወቅት እየጠበቁ እንደ አዲስ ሊጋሩ ይችላሉ።

በ7ኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ ወቅት ከተሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎች መካከል ከአውድ ውጪ ጥቅም ላይ የዋሉ  ምስሎች፣በሰው ሰራሽ አስተውሎት(AI) የተፈጠሩ ምስሎች እና በስላቅ መልክ የተሰራጩ መረጃዎች ይገኙበታል።

ከአውድ ውጪ፡ ይህ ምስል በግንቦት ወር 2018 . ደብረብርሃን ውስጥ የተዘጋ መንገድን አያሳይም

 ምስሉ ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ይገኛል።

ይህ በግንቦት ወር 2018 ዓ.ም ደብረብርሃን ውስጥ የተዘጋ መንገድን ያሳያል በሚል ኤክስ (የቀድሞ ትዊተር) ላይ ከምስል ጋር የተጋራው ልጥፍ ከአውድ ውጪ ነው።

ከምስሉ ጋር የተጋራው ጽሁፍ “መንገዶች ተዘግተዋል ፤ ከቤቶ አይውጡ! ከዛሬ ግንቦት 21/2018 ጀምሮ በአማራ ክልል ከአምቡላንሶች በስተቀር ሁሉም መንገዶች ለተሽከርካሪዎች ዝግ ናቸው። ድል ለአማራ፣ ፋኖ ሞት ለብልፅግና”  ይላል።

ጉግልን በመጠቀም የተደረገው የምስል ፍለጋ ውጤት በመጣራት ላይ ያለው ምስል በግንቦት ወር 2018 ዓ.ም ደብረብርሃን ውስጥ የተዘጋ መንገድን እንደማያሳይ አረጋግጧል።

ምስሉ ሚያዚያ 4 ቀን 2015 ዓ.ም ያለ ምንም ማብራሪያ እዚህ የፌስቡክ ገጽ ላይ ተጋርቶ ነበር።

እንዲሁም እዚህእዚህ እና እዚህ ጋር እንደሚታየው በምርመራ ላይ ያለው ምስል ከዚህ ቀደም በደብረብረሀን ከነበረ የመንገድ መዘጋት ጋር በተያያዘ በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ድረ-ገጾች ላይ ታትሞ ነበር።

ይሁን እንጂ ዲ ደብሊው ግንቦት 20 ቀን 2018 ዓ.ም ያወጣው ዘገባ “የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ መግለጫ ከነገ አርብ ግንቦት 21 እስከ መጨው ማክሰኞ ግንቦት 25 ቀን 25 2018 ዓ.ም ድረስ በአማራ ክልል ከአምቦላንስ በስተቀር ምንም አይነት የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ እንዳይኖር አሳስቧል” ይላል።

የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን) በዘመነ ካሴ ይመራ የነበረው የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል (አፋብኃ) እና በእስክንድር ነጋ ይመራ የነበረው የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) ራሳቸውን “አክስመው” የፈጠሩት አንድ ታጣቂ ድርጅት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ግንቦት 21 ቀን 2018 ዓ.ም የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የአማራ ክልል ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያን ዋቢ አድርጎ በትክክለኛ የፌስብክ  ገጹ ላይ “በሕዝብ ላይ ውዥንብር ለመፍጠር እየተላለፈ ያለው መረጃ መሬት ላይ የሌለና ፍጹም የሐሰት ነው” በማለት በአማራ ክልል መንገድ ተዘግቷል የሚለው መረጃ ሐሰተኛ መሆኑን ገልጿል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ  ባጋጠመ የጸጥታ ችግር የተነሳ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ 143 የምርጫ ጣቢያዎች ግንቦት 24 2018 ዓ.ም በተደረገው 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ላይ አለመከፈታቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማስታወቁ ተዘግቧል።

ኤ.ኤፍ.ሲ.ኤ ስልጠና  መረጃ አጣሪ ባለሞያ  በግንቦት ወር 2018 ዓ.ም ደብረብርሃን ውስጥ የተዘጋ መንገድን ያሳያል በሚል ኤክስ (የቀድሞ ትዊተር) ላይ ከምስል ጋር የተጋራውን ልጥፍ መርምሮ ከአውድ ውጪ መሆኑን አረጋግጧል።

የተቀየረ: ይህ ምስል የሃይማኖት አባት የብልጽግናን የምርጫ ምልክት ይዘው ቅስቀሳ ሲያደርጉ አያሳይም

ምስሉ ግንቦት 10 ቀን 2018 . የቤተክርስቲያን የጸበል ቤት ምርቃት ላይ ከተነሳ ፎቶ የተወሰደ ነው።

የኦርቶዶክስ የሃይማኖት አባት የብልጽግና ፓርቲ የምርጫ መወዳደሪያ ምልክት የሆነውን የስንዴ ነዶ ይዘው ያሳያል በሚል ፌስቡክ ላይ የተጋራው  ይህ ምስል የተቀየረ ነው።

ምስሉ በተለያዩ የማህበራዊ ትስስር ገጾች እየተዘዋወረ ሲሆን ፊንፊኔ ፕሬስ በተባለው የፌስቡክ ገጽ  ከምስሉ ጋር የተጋራው ልጥፍ “ድሮ መንግሰት ሰማያት ቀርባለች ንስሃ ግቡ ይሉ ነበር የሃይማኖት አባቶች….ዘንድሮ ምርጫ ቀርባለች እና ብልፅግናን ይምረጡ እያሉን ይገኛሉ” ይላል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን የሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ መረጃ የሚያቀርቡ የማህበራዊ ሚዲያ የዜና ገጾች ላይ ጉዳዩን በተመለከት የተገኘው መረጃ በመጣራት ላይ ያለው ምስል ትክክለኛ እንዳልሆነ ያሳያል።

ምስሉ ግንቦት 10  ቀን 2018 ዓ.ም ሸገር ሀገረስብከት ሚዲያ  በተባለ የፌስቡክ ገፅ  ላይ በሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት ለገጣፎ እና ለገዳዲ የተመረቀን የጸበል ስፍራን በተመለከተ ከተለጠፈ ዜና ጋር አብሮ ተጋርቶ ነበር። በትክክለኛው ፎቶ ላይ እኚህ የሀይማኖት አባት መስቀል ይዘው ይታያሉ።

ከግራ ጀምሮ: ትክክለኛው እና በመጣራት ላይ ያለው ምስል

ወዝ ኢትኤአይን (WasItAI) በመጠቀም የተደረገው ተጨማሪ ማጣራት ምስሉ 99 በመቶ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ( ኤ.አይ)  የተቀናበረ መሆኑን ያሳያል
እንዲሁም ኤፍሬም እሸቱ ኤፍሬም የተባለው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን  መምህር “የ Ai ፈተና ዓይኑን አፍጥጦ ሲመጣ” በሚል በትክክለኛው የፌስቡክ ገጹ ላይ  ባጋራው ልጥፍ በመጣራት ላይ ያለው ምስል በሰው ሰራሽ አስተውሎት  የተቀናበረ መሆኑን በማስረዳት ትክክለኛው ፎቶ የሚገኝበትን የማህበራዊ ሚዲያ ገጽ ከትክክለኛው ምስል ጋር አጋርቷል

የስንዴ ነዶ በኢትዮጵያ በግንቦት ወር 2018 ዓ.ም በሚደረገው አጠቃላይ ምርጫ ከሚሳተፉት የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አንዱ የሆነው የብልጽግና ፓርቲ የመወዳደሪያ ምልክት ነው። የ2018 የኢትዮጵያ አጠቃላይ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም  ተካሂድዋል።

ኤ.ኤፍ.ሲ.ኤ ስልጠና  መረጃ አጣሪ ባለሞያ  የኦርቶዶክስ የሃይማኖት አባት የብልጽግና ፓርቲ የምርጫ መወዳደሪያ ምልክት የሆነውን የስንዴ ነዶ ይዘው ያሳያል በሚል ፌስቡክ ላይ የተጋራውን ምስል መርምራ የተቀየረ መሆኑን አረጋግጧለች።

ስላቅ፡ ይህ ምስል በእገታ ላይ የነበሩ ዜጎች በኢትዮጵያ የተደረገ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ድምጻቸውን ሲሰጡ አያሳይም:: 

ምስሉ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤ.አይ)  የተፈጠረ ነው።
ይህ በእገታ ላይ የነበሩ ዜጎች በኢትዮጵያ የተደረገ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ድምጻቸውን ሲሰጡ ያሳያል በሚል ፌስቡክ ላይ የተጋራው ልጥፍ ስላቅ ነው።
ምስሉን ያጀበው ጽሁፍ “ከዚህ በላይ ጀኖሳይድ አለ እንዴ? በእገታ ላይ የነበሩ ዜጎች ድምፃቸውን ሰጥተው ወደ ታገቱበት ካምፕ ተመለሱ!!! ህዝቡ አልገባውም እንጅ በዓለም ታሪክ አሳፋሪ ድርጊት ነው የተፈፀመበት” ይላል።

ምስሉ ተመሳሳይ ይዘት ካላቸው ጽሁፎች ጋር እዚህ እና እዚህ ጋር እንደሚታየው በሌሎች የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች ላይም ተጋርቶ ነበር። 


ፎቶ ላይ የቃላት ግድፈቶች፣ ትርጉም የማይሰጡ አረፍተ ነገሮች እና የተፈጥሮ ይዘቱን ያልጠበቀ የግለሰብ ፊት ይታያል።  እነዚህ ግድፈቶች በሰው ሰራሽ አስተውሎት  የተቀናበሩ ምስሎች ላይ ከሚታዩ ዋነኛ ባህሪያት መካከል የሚጠቀሱ  ናቸው።

እንዲሁም ዎዝኢትኤአይ (WasItAI)  የተባለውስ በሰው ሰራሽ አስተውሎ የተሰሩ ምስሎችን ለመለየት የሚያስችለውን መሳሪያ በመጠቀም የተደረገው ተጨማሪ ማጣራት ምስሉ 88 በመቶ በሰው ሰራሽ አስተውሎ የተቀናበረ መሆኑን አረጋግጧል።

ከግራ ጀምሮ: በመጣራት ላይ ያለው ምስል እና የዎዝኢትኤአይ ውጤት

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሚደረግበት ቀን የተለያዩ የህዝብ እና መንግስት ሚዲያዎችራጭን የተመለከቱ የ ዜና ዘገባዎች ሽፋኖች ሰጥተው ነበር።የእነዚህ ሚድያዎች የዜና ዘገባዎች  ፈገግ እንዳደረጋቸው ሲገልጹ የነበሩ ዜናዎቹን ሰብስበው ሲያጋሩ  የነበሩ ገጾችም ታይተዋል። በተመሳሳይ  ሁኔታ ውስጥም ነው ይህ በመርመር ላይ ያለው  ልጥፍ  በፌስ ቡክ ላይ የተጋራው።

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀሎች በተደጋጋሚ እንደሚፈጸሙ በጉዳዩ ዙሪያ የተሰሩት ዘገባዎች ያሳያሉ። ወንጀሉ በአብዛኛው እንደ ገቢ ማስገኛ የተወሰደ መሆኑን የሚጠቅሰው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን  ድርጊቱ “በተደጋጋሚ፣ በተንሰራፋና በተደራጀ መልኩ እንደሚፈጸም፤ አልፎ አልፎም እንደ በቀል፣ ለፖለቲካ ዓላማ ወይም የታገተ ሌላ ሰውን ለማስለቀቅ በሚል በአጸፋ መልኩ የሚፈጸም መሆኑን” አመልክቷል። ኮሚሽኑ የዜጎች የመንቀሳቀስ መብት እንዲከበርመግለጫው ጠይቆ ነበር።

በተለያዩ ጊዜያት የተፈጸሙት እገታዎች በተለይም በጭነት ተሽከርካሪዎች እና በህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ላይ እንደሚበዛ በእዚህ የቢቢሲ ዘገባ ላይ ተጠቅሷል። 

ኤ.ኤፍ.ሲ.ኤ ስልጠና  መረጃ አጣሪ ባለሞያዋ በእገታ ላይ የነበሩ ዜጎች በኢትዮጵያ የተደረገው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ድምጻቸውን ሲሰጡ ያሳያል በሚል ፌስቡክ ላይ የተጋራው ልጥፍ መርምራ ልጥፉ ስላቅ መሆኑን አረጋግጣለች። የእውነታ ምርመራው የተዘጋጀው በአዲስ ጊዜ  ሲሆን አፍሪካን ፋክት ቼኪንግ አሊያንስስ (ኤ.ኤፍ.ሲ.ኤ) የዘርፉ ባለሞያዎችን ለማብቃት የሚሰራው ስራ አካል ነው። ጥንቅሩ ከተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ቀንድ የልዩ መልእክተኛ ቢሮ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ከኮድ ፎር አፍሪካ፣ ፔሳቼክ ጋር በተደረገ የአቻ ለአቻ ስልጠና ላይ ተመስርቶ የተዘጋጀ ነው።  የኤ.ኤፍ.ሲ.ኤ  ስልጠና የተመራማሪዎችን  ሆነ የጋዜጠኝነት ነፃነት ባከበረ መልኩ ሲሆን ላቅ ያሉ የምርመራ ዘዴዎችን እና መሳሪያዎችን ተደራሽ ያደርጋል።