ለፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አቤቱታ ያቀረቡት ሶስት ጋዜጠኞች ከእስር ተፈቱ። ዛሬ እና ከትላንት በስቲያ ቅዳሜ ከእስር የተለቀቁት ጋዜጠኞች በቃሉ አላምረው፣ በላይ ማናዬ፣ ቴዎድሮስ ዘርፉ ናቸው።
በትናንትናው ዕለት ከእስር የተፈቱት ሶስቱ ጋዜጠኞች የፌደራል ፖሊስ “ሕገ መንግስታዊ መብታቸውን በመጣስ በእስር እንዲቆዩ” ማድረጉን በመጥቀስ ለፍርድ ቤት “አካልን ነጻ የማውጣት” አቤቱታ ያቀረቡት ባለፈው ሳምንት ነበር። ከአቤቱታ አቅራቢዎች አንዱ የሆነው የ“ኢትዮ ኒውስ” የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን መስራች እና አዘጋጅ የሆነው ጋዜጠኛ በላይ ሰኞ ሰኔ 10፤ 2016 የተፈታ ሲሆን አስር ወራትን በአዋሽ አርባ ወታደራዊ ካምፕ በእስር ያሳለፈው ሌላኛው ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ፤ ባለፈው አርብ ሰኔ 7፤ 2016 ወደ አዲስ አበባ እንዲመጣ ከተደረገ በኋላ በማግስቱ ከእስር ተፈቷል፡፡“ምኒልክ” እና “ዓባይ”በተሰኙ የበይነ መረብ እና የሳተላይት ቴሌቪዥን ቻናሎች ላይ በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ፕሮግራም ያዘጋጅ የነበረው ቴዎድሮስ፤ በፖሊስ ቁጥር ስር የዋለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በፓርላማ ከጸደቀ ከአንድ ሳምንት በኋላ ነበር።
ከአማራ ክልል በተጨማሪ እንዳስፈላጊነቱ “በየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ” ተፈጻሚነት እንዲኖረው የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፤ በመጀመሪያ ከተቀመጠለት የስድስት ወራት የጊዜ ወሰን በተጨማሪ አራት ወራት ተራዝሞ እንደነበር አይዘነጋም። “በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሰውን ኃይል ትደግፋለህ” በሚል ምክንያት በፖሊስ መያዙን የሚገልጸው ጋዜጠኛው፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የጊዜ ገደብ ከተጠናቀቀ በኋላም ለ10 ቀናት በእስር ላይ ቆይቷል።
ጋዜጠኛው ባለፈው ሳምንት አርብ ከአዋሽ አርባ አዲስ አበባ ወደሚገኘው የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ እንዲመጣ ከተደረገ በኋላ፤ “የሲቪል ልብስ በለበሱ” ሁለት ግለሰቦች ጥያቄዎች እንደቀረቡለት ገልጿል። “ምርመራ ይሁን፤ ምን ይሁን በማታውቀው ሁኔታ ቢሮ ላይ ጠርተው ያነጋግሩሃል” የሚለው ጋዜጠኛው፤ በሁለቱ ሲቪል ግለሰቦች የህይወት ታሪኩን መጠየቁን ጠቁሟል።
በዚህ ጊዜ ሁለቱ ግለሰቦች “ለእኛ እንደተመደቡልን፣ ኮምዩኒኬት እንደሚያደርጉን እና ወደ ፊትም እንደሚያገኙን ነግረውናል” ያለው ቴዎድሮስ፤ ከእስር ከተለቀቀ በኋላ “ስልኩን እንዳይዘጋ” እንደተነገረው ጨምሮ ገልጿል። ከቴዎድሮስ ጋር በተመሳሳይ ቀን ወደ አዲስ አበባ እንዲመጣ የተደረገው፤ ጋዜጠኛ በቃሉም ተመሳሳይ ጥያቄዎች እንደቀረቡለትም አክሏል።
“አልፋ ሚዲያ” የተሰኘው የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን መስራች እና አዘጋጅ የሆነው ጋዜጠኛ በቃሉ፣ የታሰረው የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ ውሳኔ ካሳለፈ ከሁለት ቀናት በኋላ ነበር። በቃሉ ከሐምሌ ወር መጨረሻ ጀምሮ ለአምስት ወራት በአዋሽ አርባ ወታደራዊ ካምፕ ታስሯል።
ጋዜጠኛው ባለፈው ጥር ወር መጀመሪያ ላይ ለህክምና ወደ አዲስ አበባ እንዲመጣ የተደረገ ቢሆንም፤ “ህክምናውን ሳይጨርስ” በሚያዝያ ወር አጋማሽ በድጋሚ ወደ አዋሽ አርባ ተወስዶ ነበር፡፡ በቃሉ ወደ አዲስ አበባ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ባለፈው አርብ በድጋሚ እንዲመጣ ከተደረገ በኋላ በትናንትናው ዕለት ተፈቷል፡፡
