“ሁለት ጊዜ ምዘና ያላለፉ ሰራተኞች  ይሰናበታሉ፡፡”አዲሱ የሰራተኞች ረቂቅ አዋጅ

አዲሱ የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች ረቂቅ አዋጅ ትናንት ማክሰኞ ግንቦት 6/2016 ዓ.ም. ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ውይይት ተካሄደበት።

 17 ክፍሎች እና በ160 አንቀጾችየያዘው ይህ ረቂቅ  አሁን በስራ ላይ ካለው አዋጅ አንጻር ዝርዝር ጉዳዮችን የያዘ እና ከዚህ ቀደም በሌላ አዋጅ ይሸፈኑ የነበሩ ጉዳዮችን ያካተተ ነው ተብሏል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከታህሳስ ወር ጀምሮ ነባር ሰራተኞች ላይ አዲስ ድልድል ሲያከናውን በመስፈርትነት የተጠቀማቸው የምዘና እና ሕብረ ብሔራዊነት እና አካታችነት ጉዳይም በረቂቁ ተካትተዋል።

አዲስ አዋጅ ሲዘጋጅ ለማሳካት ከታቀዱ ዓላማዎች ውስጥ አንዱ “በመንግሥት መስሪያ ቤት የሚሰጡ አገልግሎቶችን ለማስፈፀም ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎች ለማግኘት እና በሥራ ላይ ያሉትንም ለማቆየት” የሚለው አንዱ እንደሆነ በረቂቁ መግቢያ ላይ ተጠቅሷል።

ለዚህም፤ “የመንግስት ሠራተኞች የብቃት ምዘናና ማረጋገጫ ሥርዓትን መዘርጋት” አስፈላጊ እንደሆነ ይህ የረቂቁ ክፍል ያስረዳል።

በስራ ላይ ባለው የፌደራል መንግስት ሠራተኞች አዋጅ ላይም የተደነገገው የስራ አፈጻጸም ምዘና በረቂቅ አዋጁ ላይ የጊዜ ገደብ ተቀምጦለታል።

በረቂቅ አዋጁ መሰረት ማንኛውም የመንግስት መስሪያ ቤት የሰራተኞቹን “የብቃት ክፍተት” ለመለየት እና ለሰራተኞቹ “የብቃት ዳሰሳ እንዲደረግ” የመከታተል ኃላፊነት ተጥሎበታል።

መስሪያ ቤቶች “ለሥራ ብቁ የሆነን ሠራተኛ በብቃት መመዘኛ መስፈርቶቹ አማካይነት የማረጋገጥ” ስራ እንደሚያከናውኑ የሚገልጸው ረቂቁ፤ የመንግስት ተቋማቱ በስራ ላይ የሚመድቡት “በብቃት ምዘናው ዝቅተኛ ማለፊያ ውጤት ያገኘ ሠራተኛን” እንደሚሆን አስፍሯል።

“የሥራ ብቃት ክፍተት” ያለባቸው ሰራተኞች “አጭር ሥራ ተኮር ወይም ሞጅላር ስልጠና ወይም በመደበኛ ብቃት ማሟያ ረጅም ጊዜ ትምህርት” እንደሚያገኙ እንደሚደረግ በረቂቁ አዋጅ ላይ ተጠቅሷል።

“ክፍተት” የታየባቸው ሰራተኞች እነዚህን ስልጠናዎች ከወሰዱ በኋላ “የብቃት ምዘና” እንደሚወስዱ በረቂቁ ላይ ያሰፈረ ሲሆን መስሪያ ቤቶች “ከሥልጠናው በኋላ በብቃት ምዘናው አነስተኛ ማለፊያ ውጤት ያገኘውን ሠራተኛ በሥራ ላይ” እንደሚመድቡ አስቀምጧል።

ረቂቅ አዋጁ፤ “የብቃት ክፍተት ማሟያ ሥልጠና ተሰጥቶት በስድስት ወር ለሁለት ጊዜ የብቃት ምዘና አነስተኛ የማለፊያ ውጤት ያላገኘ ሠራተኛ” ይህ ረቂቅ አዋጁ ባሰፈረው መሰረት “መብቱ ተጠብቆ አገልግሎትን ስለማቋረጥ የተደነገገው ተፈጻሚ ይደረጋል” ሲል ፈተናውን ያላለፉ ሰራተኞች እጣ ፋንታ ይገልጻል።

መስሪያ ቤቶች በሚያከናውኑት የብቃት ምዘና ውጤትን መሰረት ያደረገ ምደባ መሰረት “በሥራ ላይ ለመመደብ ፍላጎት የሌለው ነባር ሰራተኛ” ላይም ከስራ የመሰናበት ተፈጻሚ እንደሚሆን ተቀምጧል።

በዚህ አይነት መልኩ የሚሰናበት ነባር የመንግስት ሰራተኛ ጡረታ ለመውጣት እድሜው ያልደረሰ ከሆነ የሁለት ዓመት የተጣራ ደመወዙ “በአንድ ጊዜ” እንደሚከፈለው ረቂቅ አዋጁ ያስረዳል። የሚሰናበት ሰራተኛ ከመስሪያ ቤቱ የሚያገኘው ይህ ክፍያ ከ12 ሺህ ብር ማነስ እንደሌለበት ተጠቅሷል።

ከዚህ በተጨማሪ የመንግስት መስሪያ ቤቶች በስራ ላይ ባለው አዋጅ የተሰጣቸውን ሰራተኛ ለመቅጠር ማስታወቂያ የማውጣት፣ የመመልመል እና የመምረጥ ኃላፊነት በረቂቁ የፌዴራል መንግስት ሠራተኞች አዋጅ ይነጠቃሉ።

በረቂቁ መሰረት ይህ ኃላፊነት የሚሰጠው እንደ አዲስ በሚቋቋመው “የኢትዮጵያ የሥራ ብቃትና አመራር ኢንስቲትዩት” ነው።

በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግስት ተቋቁሞ እስካሁን ድረስ በስራ ላይ ያለውን “የኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት” የሚተካው አዲሱ ተቋም፤ በዚህ ረቂቅ በተለይ በመንግስት ሰራተኞች ቅጥር ላይ ወሳኝ ሚና ተሰጥቶታል።

በረቂቅ አዋጁ መሰረት የመንግስት መስሪያ ቤቶች ክፍት የስራ መደብ ሲኖራቸው የሚያስታውቁት ለአዲሱ የኢትዮጵያ የሥራ ብቃትና አመራር ኢንስቲትዩት ነው።

ኢንስቲትዩቱም፤ “ማስታወቂያ በማውጣት አዲስ አመልካች እና ነባር መንግሥት ሠራተኛ እንዲመዘገብ” የማድረግ ኃላፊነት ተሰጥቶታል።

ኢንስቲትዩቱ ከተመዘገቡ ስራ ፈላጊዎች ውስጥ “አወዳድሮ አብላጫ ውጤት ያመጡትን ከቅጥር በፊት የቴክኒካል እና የባህርያዊ ብቃት ሥልጠና” እንደሚሰጥ በረቂቁ ላይ ሰፍሯል።

ከዚህ ስልጠና በኋላ ስራ ፈላጊው ግለሰብ “በመንግስት መስሪያ ቤት ለመቀጠር በኢንስቲትዩቱ የሚሰጠውን የቴክኒካል እና የባህርያዊ ብቃት ምዘና አነስተኛ የማለፊያ ውጤት ማግኘት አለበት” ሲል ረቂቅ አዋጁ ቀጣዩን የቅጥር ሂደት ያስረዳል።

ይህንን ውጤት ያስመዘገቡ ሰልጣኞች የኢንስቲትዩቱን የብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት እንደሚያገኙ ያሰፈረው ረቂቅ፤ ይህ የምስክር ወረቀት የሌለው ግለሰብ “በመንግስት መስሪያ ቤት ለመቀጠር አይችልም” ሲል ቅድመ ሁኔታ መሆኑን ያስቀምጣል።

“የነባር ሠራተኛ ወይም የዝግጁነት ሰልጣኝ የሥራ ቅጥር አመልካች ተፈላጊ ችሎታ ማሟላታቸውን እና የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ያላቸው መሆኑን በማረጋገጥ እና በማወዳደር ኢንስቲትዩቱ ቅጥር መፈጸም አለበት” ሲል ቅጥሩን መስሪያ ቤቶቹ እንዳማይፈጽሙ ይጠቁማል።

ረቂቁ እንደሚያስረዳው፤ በዚህ መልኩ የተቀጠረ የመንግስት ሰራተኛ ለስድስት ወራት በሙከራ ጊዜ ላይ የሚቆይ ሲሆን ይህ ጊዜ ሲሞላ “የሥራ አፈጻጸም ምዘና ውጤቱ ከመካከለኛ በታች ሆኖ ከተገኘ የሙከራ ጊዜው ለተጨማሪ ሦስት ወር ሊራዘም ይችላል።”

ረቂቁ፤ “በተራዘመው የሙከራ ጊዜ ውስጥ ሠራተኛው መካከለኛ ወይም ከዚያ በላይ የተጠቃለለ የሥራ አፈጻጸም ምዘና ውጤት ካላገኘ ከሥራ ይሰናበታል” ሲል አዲስ ሰራተኞች በቅጥር ለመቀጠል የሚያስፈልጋቸው ማለፊያ እንደ ነባር ሰራተኞች “አነስተኛ ማለፊያ ውጤት” አለመሆኑን ይጠቁማል።

ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የፌደራል መንግስት ሰራተኞች ረቂቅ አዋጅ ከሚያስተዋውቃቸው ለውጦች ውስጥ አንዱ የደመወዝ ስኬል ማስተካከያ በምን ያህል ጊዜ እንደሚደረግ ማስቀመጡ ነው።

በስራ ላይ ያለው አዋጅ የመንግስት ሰራተኞች የደመወዝ ስኬል “የመንግስትን የፋይናንስ አቅም፣ የህዝቡን አጠቃላይ የኑሮ ሁኔታ፣ የዋጋ ደረጃዎች እና አግባብነት ያላቸውን ሌሎች ሁኔታዎች ባገናዘበ መንገድ” እየተጠና እንደሚወሰን ይደነግጋል።

ይሁንና አዋጁ “በየጊዜው እየተጠና የሚወሰን ይሆናል” እንዲሁም “አስፈላጊ ሆኖ” ሲገኝ የደመወዝ ስኬል ተጠንቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደሚቀርብ ከመደንገግ ውጪ ይህ ጥናት በምን ያህል ጊዜ እንደሚደረግ አያስቀምጥም።

አዲሱ ረቂቅ አዋጅ በአንጻሩ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን “የሥራ ደረጃ መነሻ ዝቅተኛ ደመወዝ እና ከፍተኛ ደመወዝ ጣሪያ በየአራት አመቱ አጥንቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አቅርቦ” እንደሚያስወስን እንዲሁም አፈጻጸሙን እንደሚቆጣጠር ያስቀምጣል።

ኮሚሽኑ የሚያደርገው የአበል ማስተካከያም በተመሳሳይ የጊዜ ገደብ ተቀምጦለታል። በረቂቅ አዋጁ፤ “የመንግስት ሠራተኛ ወጪን መሸፈን የሚያስችል ልዩ ልዩ የአበል አይነቶች እና የቀን ውሎ አበል ማስተካከያ በየሁለት አመት ኮሚሽኑ ይወስናል” ሲል በየስንት ጊዜው ማስተካከያ እንደሚደረግ ይወስናል።

የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የደመወዝ ስኬልን ለማስተካከል በየአራት ዓመቱ የሚያደርገውን ጥናት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ከማቅረቡ አስቀድሞ ግን ማረጋገጫ የመስጠት ኃላፊነት ያለው አዲስ ቦርድ በረቂቅ አዋጁ ተዋውቋል።

“የሜሪት እና የደመወዝ ቦርድ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ቦርድ፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰብሳቢነት የሚመራ ይሆናል። ቦርዱ ሰብሳቢውን ጨምሮ ስምንት አባላት ያሉት ሲሆን የፕላን እና ልማት እንዲሁም የገንዘብ ሚኒስትሮች አባል እንደሚሆኑ የቦርዱን መቋቋም በሚያትተው የረቂቁ ክፍል ላይ ተዘርዝሯል።

ከቦርዱ ኃላፊነቶች ውስጥ አንዱ፤ “የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ ስኬል ማስተካከያ፣ የደመወዝ ጭማሪ፣ የክፍያና ጥቅማ ጥቅም እና ማትጊያ ወይም ማበረታቻ ጥናትን ተመልክቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረብ ያለበትን የኮሚሽኑን ውሳኔ ሀሳብ ያረጋግጣል” የሚል ነው።

የመንግስት ሰራተኞች “ከተሰማሩበት ሙያ ምድብ አንጻር መክፈል ያለባቸውን ተስማሚ፣ ተመጣጣኝ ደሞዝ እና ጥቅማ ጥቅምን“ የሚመለከት የኮሚሽኑ የውሳኔ ሀሳብም “ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ” የሚቀርበውም በቦርዱ አማካኝት እንደሆነ ረቂቁ ላይ ሰፍሯል።

በአፈጻጸም ግንባር ቀደም የሆኑ የመንግስት መስሪያ ቤቶች እና የመንግስት ሠራተኞች የሚሸለሙበትን “የአመታዊ አገልጋይነት ቀን ሽልማት ሥርዓት” መዘርጋትም ከቦርዱ ኃላፊነቶች መካከል ነው።