“በግጭቱ እየደረሰ ያለው እጅግ አሠቃቂ ጉዳት ከዚህ የበለጠ ከመባባሱ እና የበለጠ ጉዳት ከማድረሱ በፊት መፍትሔ ይሰጠው ” ኢሰመኮ

አሸናፊ አሰበ

27/03/2016

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአማራ ክልል፣ በአዊ ብሔረሰብ ዞን፣ በአየሁ ጓጉሳ ወረዳ እና በምዕራብ ጎጃም ዞን፣ ቡሬ ዙሪያ ወረዳ፤ እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ አሶሳ ዞን፣ ኦዳ ብልድግሉ ወረዳ፤ በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል፣ በአርሲ ዞን፣ ሸርካ ወረዳ እና በቄለም ወለጋ ዞን፣ ጊዳሚ ወረዳ በሲቪል ሰዎች ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶችን በተመለከተ መግለጫ አውጥቷል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ አሶሳ ዞን፣ ኦዳ ብልድግሉ ወረዳ ሥር በሚገኙ ቤልሚሊ፣ አልከሻፊ እና ቤላደሩ ቀበሌዎች በሚኖሩ የቤኒሻንጉል ብሔር ተወላጆች እና አብረው በሚኖሩት የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ላይ ኅዳር 19 ቀን 2016 ዓ.ም. ከንጋቱ 11፡00 ሰዓት ጀምሮ እስከ ቀኑ 5፡00 ሰዓት አካባቢ በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ ኦነግ-ሸኔ) በተፈጸመ ጥቃት 17 ሰዎች ሲገደሉ 7 ሰዎች ላይ ከባድ ጉዳት ደርሷል ሲል በመግለጫው ገልጿል።

በኦሮሚያ ክልል በአርሲ ዞን፣ ሸርካ ወረዳ ኅዳር 13 ቀን 2016 ዓ.ም. በጢጆ ለቡ ቀበሌ በግምት ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት በኋላ ማንነታቸው በውል ያልተለየ ታጣቂዎች በፈጸሙት ብሔር/ማንነት ተኮር ጥቃት 7 (ሰባት) የአንድ ቤተሰብ አባላት እና ሦስት ጎረቤቶቻቸው ጨምሮ በአጠቃላይ 10 (አስር) ሰዎችን መገደላቸው ተመላክቷል።

በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን፣ ቡሬ ዙሪያ ወረዳ፣ ፈጣም ሰንቶም እና በቆጣቦ ቀበሌዎች ጥቅምት 30 ቀን 2016 ዓ.ም. እና በኅዳር 1 ቀን 2016 ዓ.ም. ኢመደበኛ የአማራ ታጣቂዎች መሆናቸው የተገለጸ ቡድኖች በሰነዘሩት ብሔር ተኮር ጥቃት እና ይህንኑ ተከትሎ በተፈጠረው ግጭት በርካታ ሰዎች ላይ የሞት፣ የአካልና የንብረት ጉዳት ደርሷል ተብሏል።

የመግለጫውን ሙሉ ቃል ያንብቡ
https://ehrc.org/?p=26158