በሀገራዊ ምክክሩ ላይ አዲስ አበባን የወከሉ ወኪሎች የምክክር አጀንዳዎችን ለኮሚሽኑ አስረከቡ

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን እና የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በመወከል በሀገራዊ ምክክር የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ሲሳተፉ የቆዩ ተወካዮች ዛሬ ማክሰኞ ግንቦት 27፣ 2017 በአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም የመሰብሰቢያ አዳራሽ በተካሄደ የርክክብ ስነ ስርዓት፤ ፤ በሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ላይ “ሊመከርባቸው ይገባሉ” ብለው የመረጧቸውን ጉዳዮች ለሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ምክር ቤት አስረከቡ።

ተወካዮቹ አጀንዳዎቻቸውን በስምንት ርዕሰ ጉዳዮች በመከፋፈል  ያቀረቡ ሲሆን ከእነዚህ ርዕሰ ጉዳዮች መካከል የአዲስ አበባ ባለቤትነት እና አወቃቀር፣ ቋንቋ፣  ታሪክ እና ትርክት፣ የሃገረ መንግስት ግንባታ እና የሃገር አንድነትን፣ የአንድነት እና ብዝሃነትን የሰንደቅ አላማ እና የህገ መንግስት ጉዳዮችን የተመለከቱ ይገኙበታል ተብሏል።

አሁን በስራ ላይ ካለውን የኢፌዲሪ ህገ መንግስት ጋር የሚያያዙ፣ ተወካዮቹ የተመረጡበት የአዲስ አበባ ከተማ ጉዳይን በቀጥታ የሚመለከቱ፣ ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር ባላት የውጭ ግንኙነት ጉዳይ ላይ የሚያጠነጥኑ የአጀንዳ ርዕሰ ጉዳዮችም ለምክክር ከተመረጡት ውስጥ እንደሚገኙበት በሂደቱ የተሳተፉ ተወካዮች አስረድተዋል። የተቋማት ግንባታ፣ የምጣኔ ሀብት፤ ማህበራዊ እና ባህል ርዕሰ ጉዳዮችም እንዲሁ በአጀንዳነት መያዛቸውን ተወካዮቹ አብራርተዋል።  

ተወካዮቹ መዲናይቱን ወክለው የምክክር አጀንዳዎችን ያስረከቡት፤ ላለፉት ሰባት ቀናት በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ ሲካሄድ በቆየው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ ሲሳተፉ ከቆዩ በኋላ ነው። በአጀንዳ ማሰባሰቡ የመጀመሪያዎቹ ሶስት ቀናት፤ ከአዲስ አበባ ከተማ 119 ወረዳዎች በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተወከሉ ከሁለት ሺህ በላይ ሰዎች ተሳትፈዋል። 

እነዚህ ተሳታፊዎቹ የወከሏቸው የህብረተሰብ  ክፍሎች፤ የመንግስት እና የግል ተቋማት ሰራተኞች፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣መምህራን፣  ፣ የተገለሉ ማህበረሰቦች፣ ተፈናቃዮች እና የህብረተሰብ መሪዎችን እንደሆነ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ አስታውቋል። ተወካዮቹ በግዮን ሆቴል በነበራቸው የሶስት ቀናት ቆይታ፤ በ22 ቡድን ተከፍለው ከየህብረተሰብ ክፍላቸው ያመጡትን አጀንዳዎችን የመለየት እና የማደራጀት ስራዎችን ሲያከናውኑ ቆይተዋል።

በእነዚህ ተሳታፊዎች የተመረጡ 121 ተወካዮች ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመጣመር ከእሁድ ግንቦት 25 ጀምሮ“የአዲስ አበባ ከተማ አጀንዳዎች ናቸው” ያሏቸውን ሃሳቦች ለይተዋል። በቡድን በቡድን በመሆን በተካሄደው በዚህ የአጀንዳ መለየት ሂደት ከተሳተፉት ተወካዮች መካከል፤ በአዲስ አበባ ከተማ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፖርቲዎች፣ በአዲስ አበባ ከተማ ከተመዘገቡ ተቋማት እና ማህበራት የተወከሉ ግለሰቦች ይገኙበታል። የመንግስት ተወካዮች እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችም በዚህ ሂደት ተሳታፊ ነበሩ፡፡